ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ (ጥር ፮ ቀን ፲፰፻፲፩ ዓ.ም. - ሚያዝያ ፮ ቀን፲፰፻፷ ዓ.ም.) ከ፲፰፻፵፯ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታችው ድረስ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበሩ። በትውልድ ስማቸው ካሳ ሃይሉ ሲባሉ፣ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፣ በወታደራዊ ስማቸው መይሳው ካሳ እና እንዲሁም አንድ ለናቱ ተብለው የሚታወቁ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ወታደርና ፖለቲከኛ ነበሩ።
ቴዎድሮስ ጥር ፮ ቀን ፲፰፻፲፩ ዓ.ም. ሻርጌ በተባለ ቦታ ቋራ ውስጥ፣ ከጎንደር ከተማ በስተ ምዕራብ ተወለዱ። የተወለዱትም አገሪቷ በባላባቶች ተከፋፍላ በምትመራበት-ዘመነ መሳፍንት በሚባለው ወቅት ነበር። አባታቸው ደጃዝማች ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ የቋራ ገዢ ነበሩ። ዓፄ ቴዎድሮስ በህጻንነታቸው የቄስ ትምህርት ከቀሰሙ በኋላ፣ የአጎታቸውንና በኋላም ለጥቂት ጊዜ የጎጃሙን ጦር መሪ የጎሹ ዘውዴን ጦር ተቀላቀሉ። በዚሁ የውትድርና ዘመናቸው ከፍተኛ ችሎታን ማስመዝገብ ስለጀመሩና ዝናቸው ስለተስፋፋ በ፲፰፻፴፱ ዓ.ም. በወይዘሮ መነን ሊበን አምዴ አነሳሽነት የልጇን የራስአሊ አሉላን ልጅ፣ ተዋበች አሊን ተዳሩ ፤ እንዲሁም በደጃዝማችነት ማዕረግ የቋራ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ። ቴዎድሮስ ግን በ፲፰፻፵፬ ዓ.ም. አጠቃላይ የዘመነ መሳፍንት ሥርዓትን በመቃወም በሰሜናዊ ባላባቶች ላይ ዘመቻ ጀመሩ።
በኒህ ተከታታይ ዘመቻወች የገጠሟቸውን ባላባቶች ስላሸነፉ፣ መጀመሪያ የራስ ማዕረግን በኋላም የንጉሥ ማዕረግን በአንድ ዓመት ውስጥ ተቀዳጁ። በየጊዜው በሚያደርጉት የተሳካ ዘመቻ የዘመኑን ባላባቶች ኃይል በመሰባበር የካቲት ፫ ቀን ፲፰፻፵፯ ዓ.ም ንጉሥ ካሳ - ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆኑ። ሥርዓተ ንግሡ የዘመነ መሳፍንት መቃብር በመሆን የዘመናዊ ኢትዮጵያን ታሪክ "ሀ" በማለት ጀመረ። ዓፄ ኃይለ ስላሴ
እስከ ፈጸሙት ድረስ ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ሥራም በዚሁ ወቅት ተጀመረ። ዓፄ ቴዎድሮስ ሰሜናዊ ኢትዮጵያን ብቻ
ሳይሆን አንድ ለማድረግ የሞከሩት፣ አጠቃላይ በታሪክ የሚታወቀውን የኢትዮጵያ ክፍል ነበር - ለዚህም ዋቢ ወደ ወሎና ወደ ሸዋ ያደረጓቸው ዘመቻወች ይጠቀሳሉ።
No comments:
Post a Comment