Saturday, May 5, 2012

ሚያዚያ 27-የድል በአል


“ይህ የምትሰሙት ድምጽ የኔ የንጉሳችሁ የቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ ነዉ። አባቶቻችን ደማቸዉን አፍሰዉ ዐጥንታቸዉን ከስክሰዉ በነፃነት ያቆዩልን አገራችንን ወደ ከፍተኛዉ የሥልጣኔ ደረጃ ለማራመድ የምንደክምበት ጊዜ ከጥንት ዠምሮ ስለሆነ ደመኛ ጠላታችን ኢጣሊያ ይህንን እይታ ወሰናችንን ጥሳ የግፍ ጦርነት እንዳደረገችብን ሁላችሁም የምታዉቁት ነዉ። እኛም በተቻለን ከተከላከልን በሗላ ርዳታ ለመጠየቅ ወደ መንግስታት ማሕበር ወደ ወዳጆቻችን መንግስታቶች መጣን እዚህ ስንነጋገር በቆዬንበት  ጊዜ የኢትዮጵያ አርበኞች ሰይፋችሁን ሳትከቱ ፊታችሁን ሳትመልሱ ሰንደቅ ዐላማችሁን ሳታጥፉ ለባዕድ አንገዛም በማለት በመሳሪያ ብዛት ከሚበልጣችሁ ጨካኝ ጠላት ጋር የባሕርይ የሆነዉን ዠግንነታችሁን መሣሪያ አድርጋችሁ  በኢትዮጵያ አምላክ ብቻ ተማምናችሁ በዠግንነት ቀንና ሌሊት በዱር በገደል ስትጋደሉ ቆይታችሁ ይኸዉ አሁን እንደምታዩት የማያቋርጥ የአምስት አመት ትግላችሁ የድካማችሁንና የመሥዕዋታችሁን ፍሬ ለማየት እንድትበቁ አደረጋችሁ።

 የሀገሬ የኢትዮጵያ ህዝብ!
ዛሬ ኢትዮጵያ እጆቹዋን ወደ እግዚያብሔር ዘርግታ እልል እያለች ምስጋናዋን የምታቀርብበት ደስታወንም ለልጆቹዋ የምትገልጽበት ቀን ነዉ።  የኢትዮጵያ ልጆች  ከባድ የመከራ ቀንበርና ከዘለአለም ባርነት ነፃ የወጡበት ቀንና እኛም አምስት አመት ሙሉ ተለይተነዉ ከነበረዉ ከምንወደዉና ከምንናፍቀዉ ሕዝባችን ጋር ለመቀላለቀል የበቃንበት ቀን ስለሆነ ይህ ቀን የተከበረና የተቀደሰ በያመቱም ታላቁ የኢትዮጵያ በዓል የሚዉልበት ነዉ። በዚህም ቀን ለሚዎዷት ላገራቸዉ ነፃነት ለንጉሰ ነገስታቸዉና ለሰንደቅ ዐላማቸዉ ክብር ካባቶቻቸዉ የተላለፈዉን ጥብቅ አደራ አናስዎስድም በማለት መስዕዋት ሆነዉ ደማቸዉን ያፈሰሱትን አጥንታቸዉን የከሰከሱትን ዠግኖቻችንን እናስታዉሳለን። ለዚህም ለዠግኖቻችን የኢትዮጵያ ታሪክ ምስክር ይሆናል።  

ባለፈዉ አምስት አመታት ዉስጥ በዝርዝር ተነግረዉና ተቆጥረዉ የማያልቁ ያገኘናቸዉ መከራና ስቃይ ትምህርት ሆነዉን ሰራተኛነት አንድነት ህብረትና ፍቅር በልባችሁ ተጽፈዉ ለምናስበዉ ለኢትዮጵያ ጉዳይ ረዳቶች ለመሆን ዋና ትምህርት የሚሰጣችሁ ነዉ። ባዲሷ ኢትዮጵያ ከእንግድህ ወድያ የማትነጣጠሉ በሕግ ፊት ትክክልና ነፃነት ያላችሁ ሕዝቦች እንድትሆኑ እንፈልጋለን። አገር የሚለማበትን ሕዝብ የሚበለጽግበትን እርሻ፣ ንግድ፣ ትምህርትና ጥበብ የሚሰፋበትን የሕዝባችን ሕይዎቱና ሀብቱ የሚጠበቅበትን የአገር አስተዳደርም ባድሱ ስልጣኔ ተለዉጦ ፍጹም የሚሆንበትን ይህን ለመሰለዉ ለምንደክምበት ስራ አብሮ ደካሚ መሆን አለባችሁ:: [1]
                                                ***
“የኢጣሊያ መንግስት ኢትዮጵያን  ድል አድርጎ ለመያዝ ችሎት ከሰጠዉ መሳሪያ በቀር ኢትዮጵያን ለመግዛት ሌላ ተስፋ ያደረገዉ ነገር ነበር ይኸዉም የኢትዮጵያ የነገድ ልዩነት ነዉ።  የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ እርሱ አሳብ አንደኛዉ ወገን ከሴም ዘር የመጣዉ የትግሬና የሸዋ፣ የጎጃም፣ የበጌምድር፣ በጠቅላላዉ አማራ የሚባለዉ፣ ሁለተኛዉ በኢትዮጵያ ምዕራብና ደቡብ የሚገኙትን እነዎለጋ፣ እነጅማ፣ እነሲዳማ፣ እናሩሲ አነዚህን የመሳሰሉት አገሮች ከካም ዘር የመጡ በነገድም በቋንቋም በሃይማኖትም የተለያዩ ናቸዉ። አንደኛዉ ወገን ቢያምጥብኝ ሁለተኛዉን ወገን ይዤ አጠፋዋለሁ የማለት ተስፋ ነበረዉና ይህንንም ሊሰራበት እንደጣረ በጉልህ ታይቷል። ዳሩ ግን የ3ሺህ አመት ባለዉ የነፃነቱ ዘመን በታሪኩ ዉስጥ ምንም የሚያሳፍር ገጽ የሌለበት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን አሳይቶ ለጠላቱ ሳይመች ቀረ።” [2]
------------------------------------------------
[1]: ሁሌ  በየዓመቱ  በዛሬዉ እለት ሚያዚያ 27 ቀን የሚከበረዉን የድል በዓልንና የኢጣሊያን ወራሪ ሐይል በጀግኖች የኢትዮጵያ አርበኞች ብርቱ ትግል ድል መደረጉን አስመልክቶ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ  ሀይለ ስላሴ  በ1932 ሰኔ ወር ማለቂያ ላይ  ከተከታዮቻቸዉ ጋር ከስደት ተመለሰዉ የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም  ካረፉ ከሁለት ቀን በሗላ ለኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች በሬድዮ ካሰሙት ድስኩር በከፊል የተዎሰደ።

[2]: ሀገራችን ኢትዮጵያን በግፍ ከወረረ በሗላ በሀይል አምስት አመት  ይዞ የቆየዉ የኢጣሊያ ወራሪ ጦር በወቅቱ ስልጣኑ ለማራዘም ከሚያግዘዉ ዘመናዊ መሳሪያን ከታጠቁና ከሰለጠኑ ወታደሮች በጠጨማሪ ይከተል የነበረዉን ሕዝብን በዘር በመከፋፈል አንድነቱን የማሳጣት ስልትና በወቅቱ የነበረዉን የህዝብ አንድነትና የጋራ ትግል ለማስረዳት የኢትዮጵያን ታሪከ በቀዳሚነት በመመዝገብ  ከሚጠቀሱ ጥቂት ኢትዮጵያዊያንን የታሪክ ተመራማሪና ጸሐፊዎች አንዱና የምንግዜም ባለዉለታችን የሆኑት የታሪክ ተመራማሪና ጸሐፊ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ  “በኢትዮጵያ ታሪክ” መጽሐፋቸዉ የተጠቀሙበት አገላለጽ። 
---------------------------------------------
ምንጭ፡ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ /የኢትዮጵያ ታሪክ- ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ/


------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

No comments:

Post a Comment