መንግሥቱ ንዋይ በ፲፱፻፰ ዓ/ም አዲስ አበባ ላይ አራዳ ጊዮርጊስ ገዳም ሠፈር አካባቢ ተወለዱ። አባታቸው ዓለቃ ንዋይ የደብሩ ዓለቃ ነበሩ። ትምሕርታቸውን በተፈሪ መኮንን ትምሕርት ቤት
ተከታትለው አዲሱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ሲመሰረት ወደዚያ ተዛውሩ። የገነት ጦር
ትምሕርት ቤት ሲከፈት ደግሞ፣ መንግሥቱ ንዋይ ተመልምለው ከገቡት ዕጩ መኮንኖች አንዱ ነበሩ። ሌሎች (በኋላ
ጄነራሎች) እንደነ አቢይ አበበ፣ አሰፋ አያና፣ ኢሳያስ ገብረሥላሴና ከበደ ገብሬ በዚሁ ትምሕርት ቤት ከመንግሥቱ
ጋር የነበሩ ዕጩ መኮንኖች ናቸው።
መንግሥቱ ከዚያው የጦር ትምሕርት ቤት በመቶ አለቃ ማዕረግ ተመርቀው ሲወጡ ወዲያው የጠላት ኢጣልያ ጦር አገሪቱን ይወርና እሳቸው ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ወደማይጨው ዘምተው ግዴታቸውን ተውጥተዋል። ጠላትም ድሉን ሲቀዳጅ እና ንጉሠ ነገሥቱ ሲሰደዱ መቶ አለቃ መንግሥቱ በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደሸሸበት ነቀምት ሄደው እዚያ “ጥቁር አንበሳ” የሚባለውን ማኅበር መሥራች አባል ናቸው። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ከጓደኞቻቸው ጋር ወደጅቡቲ ተሰደዱ። በ፲፱፻፴፪ ዓ/ም ንጉሠ ነገሥቱ ተመልሰው ካርቱም ሲገቡ እነኚህን ስደተኛ መኮንኖች ከጅቡቲ ወደካርቱም እንዲመጡ ይደረግና መንግሥቱ ንዋይ ከነ ሙሉጌታ ቡሊ፣ ነገሠ ወልደሐና፣ ወልደማርያም ኃይሌ፣ ዘውዴ ገበሳ እና ታምራት ዘገየ ጋር ሆነው ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ተቀላቀሉ። ወዲያውም ከእሳቸው ጋር በ፲፱፻፴፫ ዓ/ም አብረው ወደኢትዮጵያ በድል ሲገቡ በክብር ዘበኛ ውስጥ በጄኔራል ሙሉጌታ ሥር ሻምበል ሆነው ቆዩ። በመስከረም ወር ፲፱፻፵፱
ዓ/ም ኮሎኔል መንግሥቱ ብርጋዴር ጄኔራል ተብለው የክብር ዘበኛ ጠቅላይ አዛዥነትን ተሾሙ። ተራማጅ እና የክብር
ዘበኛን ሠራዊት በሰገላዊ ውትድርና ንቃተ ሕሊናውን ለማዳበር ብዙ የጣሩ መኮንን እንደነበሩ ተመስክሮላቸዋል።
No comments:
Post a Comment