Wednesday, June 20, 2012

ግን ለምን እንፈራለን? (ክፍል አንድ)


የአለፈዉ ሳምንት አድስ ጉዳይ መጽሔት አብይ አርዕስት አድርጎ ይዞት የወጣዉ ሀሳብ በአሁኑ ወቅት ያሉትን የኢትዮጵያ ምሁራንን በፍርሃት ተሸብቦ የመቀመጥን ነገር ነበር።  አድስ ጉዳይ “የፍርሃት ሀገር ዜጎች፣ ‘ኦሜርታ’!” በሚል አርዕስት ይህንኑ ጉዳይ የዳሰሰበትን ማራኪ ጽሁፍ ያስነበበን ሲሆን እነዚህኑ ከልክ ባለፈ ፍርሃት ተሸብበዉ የሚገኙ የዘመናችንን ምሁራንን፣ “ዉሃ ዉስጥ ተኝተዉ የሚያልባቸዉ ምሁራን” ሲል ነበር የገለጻላቸዉ። በርግጥም አዋቂና ችግር ፈች የሚባለዉ የአንድ ሀገር የተማረ ዜጋ የራሱንና የሌሎችን መብት ለማስከበር ከመትጋት ይልቅ በፍርሃት ተሸብቦና ተሳስስሮ ከተቀመጠ ቢያንስ መብትና ግደታዉን እንኳን በቅጡ ለይቶ የማያዉቀዉ ሌላኛዉ ያልተማረ ህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ከፍርሃትም በላይ በሆነ ጭንቅ ዉስጥ እየኖረ እንደሆ መገመት አያዳግትም።


እኔም የአድስ ጉዳይን ጽሑፍ አንብቤ ከጨረስኩ በሗላ፣ ግን ለምን እንፈራለን? ስል ራሴን ጠይቄዉ ነበር። መልሱ ግን ቀላል ሆኖ አላገኘሁትምና በርግጠኝነት ይኸነዉ ማለት አልችልም። ሆኖም ግን ሀገራችን ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን  በታሪክ አጋጣሚ ለማስተዳደር እድሉን ካገኙ መሪዎች መካከል ከትልቅ እስከ ትንሽ ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ፣ ይህንኑ ዜጎችን በፍርሀት የማጥመቅና በሀገራቸዉ ፖለቲካ ተሳታፊ እንዳይሆኑ የማሴርን ሴራ በተለያየ መጠንና አይነት ሲተገብሩና ሲያስፋፉ በመኖራቸዉ ዛሬ ላይ ለደረስንበት “ፖለቲካና ኮረንቲን በሩቁ” በሚል የህይዎት ፍልስፋና ለሚመራ አንካሳ ትዉልድ አሌ የማይባል አስተዋጾ እንዳበረከቱ ግን በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ግን ለምን እንፈራለን? እስኪ “የአድሲቱ ኢትዮጵያ” መስራች እየተባሉ ከሚሞካሹት አጼ ቴዎድሮስ እንነሳና “ብልጣብልጥ” እየተባለ እስከ ሚብጠለጠለዉ ኢህአድግ ድረስ ጥቂት የታሪክ ገጾችን እያገላበጥን ዛሬ ላይ ለተጠናወተን ፍርሃት ሰበብ ይሆናሉ የምንላቸዉን አንዳንድ የታሪክ ዘበዞች እየመዘዝን አብረን እንመልከት።

 

በቅድሚያ ግን ጠቅለል ባለ መልኩ ሶስት መሰረታዊ ነጥቦችን እናስቀምጥ። አምባገነን መንግስታት ዜጎች በሀገራቸዉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ በያገባኛል ስሜት በድፍረትና በቀጥታ ተሳታፊ እንዳይሆኑ ለመከልከል የሚጠቀሙባቸዉ በርካታ ዘዴዎችና አካሄዶች አሏቸዉ። ከነዚህም መካከል መንግስትን ለመቃወም በድፍረት ቀድመዉ የሚወጡና ፊት ለፊት የሚጋፈጡ ጥቂት ደፋሮችን ለሌሎች ማሰተማሪያ ይሆኑ ዘንድ አይቀጡ ቅጣትን መቅጣት አንዱና ዋነኛዉ ሲሆን መንግስት የመለኮት ሀይል ያለዉ እስኪ መስል ድረስ የግለሰቦችን ምስጥር በማነፍነፍና በማጋለጥ ህዝብ፣ “ከነሱ አይን የሚሰወር ነገር የለም!” ብሎ እንዲያምንና  በፍርሀት እንዲሽመደመድ ማድረግ ደግሞ ሌላኛዉና ሁለተኛዉ ዜጎችን በፍርሀት ገመድ ጠርንፎ የማሰሪያ ዘዴ ነዉ። ከነዚህ ሁለት መሰረታዊ አካሄዶች በተጨማሪ የተለያዩ ልብን የሚያርዱ ፕሮፓጋንዳዎችን በካድሬዎቻቸዉ በኩል በመንዛትና ህዝብ ጆሮ እንዲደርሱ በማድረግ ዜጎች መንግስትን ከተገቢዉ በላይ አግዝፈዉ እንዲመለከቱትና በፍርሀት ተሸማቀዉ እንዲቀመጡ ማድረግ ደግሞ ሌላዉና ሶስተኛዉ የተለመደ መሳሪያ ነዉ። እዚህ ላይ ጥቂት ሁነኛ የታሪክ ማስረጃዎችን እንመልከት፤

 

አጼ ቴዎድሮስ አልባሌ ወታደር መስለዉና ያረባ ልብስ እየለበሱ ከህዝቡ መሀል በመቀላቀል ንጉሱን የሚያማዉን የተበደለዉንም በደል ከባለንጄሮቹ ጋር የሚያወጋዉን ካደመጡ በሗላ በሌላ ጊዜ ያንን ሰዉ ቤተመንግስታቸዉ ድረስ ያስጠሩና ክፉ የተናገሩንና ያማዉን ሲወቅሱና ሲጣሉት፣ መልካም የተናገረዉን ደግሞ ይሾሙት ይሸልሙት ነበር። ይህንንም ህዝቡ ባወቀ ጊዜ  አጼ ቴዎድሮስ የምንለዉን ሁሉ የትም ቦታ ሆነዉ ይሰማሉ የሚል ፍርሃት ስላደረበት ንጉሱ በአማራ አገር ሳሉ የትግሬ ሰዉ ከቤቱ ሆኖ ንጉሱን አትሙ ይሰሙናል ይል ነበር ሲሉ አንድ ያልታወቁ የአጼ ቴዎድሮስ ዜና መዋዕል ጸሐፊ በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን ነበረዉን የግለሰቦችን ምስጥር የማነፈነፍንና በፍርሃት እንድርዱ የማድረግ አካሄድ ያወሱናል። 

 

ሌላዉ የአጼ ቴዎድሮስ ዜና መዋዕል ጸሐፊ የሆኑት ደብተራ ዘነብ ደግሞ ሌላዉን የአጼ ቴዎድሮስ፣ ህዝብን በፍራት እንድርድና ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ የማድረግን አካሄድ እንድህ ሲሉ ያወጉናል። አጼ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ተብለዉ በአቡነ ሰላማ ከተቀቡ በሗላ በተለያዩ ክፍለ ሀገራት በመዘዋወርና አዋጅ በማስነገር ህዝቡን ማሰገበር ይጀምራሉ። የጁም ደረሱና የወሎን ሰዉ ግባና ገብርልኝ ቢሉት አልግብርም ብሎ በማመጽ ሽፈታ እየሆ አስቸገራቸዉ። ቴዎድሮስም የተማረከዉን ሰዉ እያስያዙ ሁለት እግሩንና ሁለት  እጁን እየቆረጡ በአንገቱ ላይ እያሰሩ ወደ ቤቱ ሰደዱት። የወሎም ሰዉ እነዚያ የተቆረጡትን ባየ ጊዜ እጅግ ደነገጠ። እንድህም አለ፣

 

ማጉረሱንስ ሚስቱ ታጉርሰዉ

ቂጡን በምን ያብሰዉ።

 

አስከትለዉም ንጉሱ ግባ ብየሀለሁ አልገባም ያልክ ለወንድ እጅና እግሩን ለሴት ደግሞ ጡቷን እቆርጣለሁ ብለዉ አዋጅ አስነገሩ። ከዚያም የወሎ ህዝብ አላህ ምን አመጣብን? ከዚህስ ጋር ማን ተዋግቶ ይተርፋል ሲል ሁሉም በጭንቅና በፍርሃት እየራደ አሜን ብሎ ገባ።

(ይቀጥላል)


------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

No comments:

Post a Comment