Friday, August 24, 2012

የመጨረሻዋን ሰዓት በቤተ መንግስት


ጥንቅር [ሞረሽ] ምድብ[ማራኪ ገፆች]

የአዳራሹ መጋረጃዎች ስላልተከፈቱ ጭልምልም ብላል። ሀይለስላሴ ዙፋናቸው ላይ ፀጥ ብለው ተቀምጠዋል። ጊዜያቸውን ሲያጣብብ የነበረው የሰው ጋጋታ ደንብና መመሪያ ማውጣት በመቆሙ አካባቢው ጭር ብሏል ። በመጨረሻ የማያውቁት ሰው ውሳኔዎችን እየሰጠ እንደሆነ ደመደሙ ።

ራስ ካሳም በበኩላቸው ፕሮቶኮሉን ጥሰው ሌሎቹ የምክር ቤት አባላት እየተከተሏቸው አዳራሹን በርግደው ገቡ ። ንጉሰ ነገስቱ በራሶቹ መምጣት አልተገረሙም ። ምንም እንኳን መረጃ የሚያቀብላቸው ሰው ባይኖርም፣ ንጉሱ ቁጣ እንደሚቀሰቅስና ያንንም ተከትሎ የምክርቤቱ አባላት ፍርሃታቸው እንደሚጨምር ያውቃሉ። 

 

“የዘውድ ምክር ቤቱ የበላይ እንደመሆኔ በቅርብ በመፈፀም ላይ ያለውን እስር በተመለከተ ምን ለማድረግ እያሰቡ እንደሆነ እንድጠይቅ ተወክያለሁ ። “

 

“ምን ለማድረግ?” አሉ ሀይለስላሴ በርጋታ “ ምንም አናደርግም።”

“ደርጉ በግርማዊነትዎ ስም እያሰረ ነው ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?”

“መርማሪ ኮሚሽኑ ጥሩ ስራ እየሰራ ነው ።”

“ይህ ሃሳብ በራሶቹ የሚደገፍ አይደለም ።”

“እናንተ የሚያስፈራችሁ ነገር የለም። እናንተ ምንጊዜም በታማኝነት ሰትሰሩ ነው የቆያችሁት።”

“ይህ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም !”አሉ ራስ ካሳ በጩኸት።

 

ሀይለስላሴ ልክ ከህልሙ እንደነቃ ሰው ተደናገጡ ። ከዚያም ወደ ረጅሙ ራስ ሄዱ። ምንም እንኳን ራሱን ቀና ብለው ቢያዩዋቸውም ግርማ ሞገሳቸው ግን እንዳለ ነበር። 

 

“የዘውድ ምክር ቤት አባላት የአካል እንቅስቃሴ (ስፖርት) መርሃ ግብር እንድኖራቸው ወስነናል።”

 

አማካሪዎች ግራ ተጋቡ ። የተናገሩትን ለመረዳት ባለመቻላቸውም እርስ በእርሳቸዉ ተያዩ። ግርማዊነታቸው በምሳሌ እየተናገሩ ይሆን ? “እውነት?” ሲሉ ራስ ካሳ ጠየቁ፡ “ግርማዊ ንጉሰ ነገስት የምርዎን አይመስለኝም ይህን የሚሉት !”

 

 “የምራችንን ነው።” አሉ ሀይለስላሴ ። “ብቃት ከሌለን እንዴት አገር ማስተዳደር እንችላለን? ስልጠናውን አሁኑኑ መጀመር አለባችሁ !”

 

ኒስካኔን[1] ቤተ-መንግስቱ ሜዳ ላይ ከአዛውንቶቹ ባለስልጣኖች ፊት ቆሟል። ንጉሰ ነገስቱ ቆመው ይመለከታሉ። ወደ ሀይለስላሴ ሲዞር ሻለቃው የእግሮቹን አውራ ጣቶች ለመንካት አጎነበሰ ።

 

የዘውድ ምክር ቤቱ አባላት ንጉሰ ነገስቱ ላይ ወዳፈጠጡት ራስ ካሳ ተመለከቱ ። ኒስካኔን ተጨነቀ ። ራሱን የጎዳቸው አካላዊ እንቅስቃሴው ሳይሆን ውርደቱ እንደሆነ አውቋል ። እንቅስቃሴውን ከመቀጠሉ በፊት ንጉሱን ዞሮ ተመለከተ ። አፄ ሀይለስላሴ ተኮሳትረዋል ። ኒስካኔን እጆቹን ወደ ላይ ከፍ ሲያደርግ አማካሪዎችም ተከተሉት ያለማመንታት በታማኝነት ። 

 

ብዙም ሳይቆዩ የምክር ቤቱ አባላት ደከሙ ። ኒስካኔንን ሊከተሉት አልቻሉም ፤ እርሱም ተጨነቀ። በመጨረሻ ራስ ካሳ ቀጥ ብለው ቆሙ ። ኒስካኔን የአካል እንቅስቃሴውን ሲደጋግመው ለመከተል ፈቃደኛ አልነበሩም ። የራስ ካሳ እንቢተኝነት ንጉሰ ነገስቱን ከቀን ህልማቸው ያነቃቸው መሰለ። 

 

 “ሻለቃ ለዛሬ የሚበቃን ይመሰለኛል” አሉ ሀይለስላሴ።

ኒሰካኔን ራሶችን አመስግኖ አቀርቅሮ ወደ ቤተ-መንግስቱ ተመለሰ።   

 

ይህንን ከላይ የሰፈረውን ታሪክ ያገኘሁት በፖል ራምባሊ ተፅፎ በትኩእ ባህታ “ሮማን የወረረ ጀግና” በሚል ርእስ ከተተረጎመው የጀግናው አትሌታችንን የአበበ በቂላን የህይወት ታሪክ ከሚያወሳው መፅሃፍ ላይ ነው ። ስለእውነት ለመናገር በዛች በመጨረሻዋ ሰአት፤ ነገሮች ሁሉ ካለቁና ከደቀቁ በሁላ አፄው ለለውጥ ሲቁአምጡ ማየት ያሰገርማል ። ይበለጡን ደግሞ ነገሩ ፈገግ የሚያሰኘው የለውጡ አንድ አካል አድርገው ያሰቡት እነዚያን አዛውንት አማካሪዎችና የዘውድ ምክር ቤት አባላት በስተርጅና (ብዙዎቹ የዘዉድ ምክርቤት አባላት እድሜአቸዉ 50ና ከዛ በላይ መሆኑን ልብ ይሏል!) ስፖርት መስራት እንዲጀምሩ ማስደረጋቸዉን መሆኑን ስናይ ነው ። አዛውንቶችን ይዘው በረሃ ሊገቡ አስበው ነበር ልበል ወይስ ሌላ ነገር አስበው ፤ በወቅቱ የነበራቸውን ሃሳብ ከሳቸው ውጭ የሚያውቅ ይኖራል ብየ አልገምትም። ያም አለ ይህ አፄው በአስራ አንደኛው ሰዓት ለለውጥ ይበጃል ያሉትን ሞክረዋል። ይህም የለውጥ እንቅስቃሴያቸው ማለት (ለአዛውንቶች የስፖርት እንቅስቃሴ መርሃ ግብር ስለቀየሱ) እሳቸውን በመሰለች ልጃቸው ልዕልት ተናኘወርቅ ሲሞካሽና ሲወደሰላቸው ነበር ። መፅሃፉን ገዝተው ቢያነቡት ዝርዝሩን ያገኙታል ። ባልና ሚሰት ከአንድ ወንዝ ይቀዳል ነበር አይደል ተረቱ ለአፄውና ለልጃቸው ግን አባትና ልጅ ከአንድ ወንዝ ይቀዳል ቢባል አንድነታቸውን ይገልፃል ።

   

_  ________________________________________________ 

[1] ኒስካኔን የታሪካዊው ጀግናችን የአበበ በቂላ አሰልጣኝ የነበረ ሲውድናዊ ነው ።

------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

No comments:

Post a Comment