Monday, May 14, 2012

እሺ! ይኸንስ የሞት ብድር ማን ይክፈለዉ?

ጎንደር-ጋይንት                                             
1970፣ እሁድ፣ ከጧቱ 4፡10
ከአጭር ጊዜ የስራ ቆይታ በሗላ ክፍለ ሀገር ወደሚኖሩት ቤተሰቦቹ በቅርቡ የተመለሰዉ ታዘበ ወልዴ፣ እንደ አረንጓዴ ስጋጃ ተዘርግቶ በተንጣለለ ትልቅ ግቢ መስክ ላይ ብርኩማ ላይ ተቀምጦ የጧት ፀሀይ እየሞቀ ነዉ። ታዘበ ከብዙ ጊዜ ድካምና ልፋት በሗላ ከአድስ አበባ ዩንቨርሲቲ በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቆ እዛዉ አድድስ አባባ ዉሰጥ የሚገኝ አንድ የመንግስት ከፈተኛ መስሪያ ቤት ዉስጥ ተቀጥሮ መስራት ከጀመረ ገና ስድስት ወሩ ነዉ። የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ በመሆኑና ቤተሰቦቹ ተምሮ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከነበራቸዉ ፅኑ ፍላጎት የተነሳ ብዙ መስዋዕትነትን በመክፈል ነበር አስተምረዉ ለዚህ ደረጃ ያበቁት። በተለይ እናቱ የወርቅዉሀ ታደሰ የእሱ ተከታይ የሆነችዉን ሴት ልጃቸዉን አመለወርቅ ወልዴን በጀርባቸዉ አዝለዉ፣ በአንድ እጃቸዉ የዉሀ መቅጃ በሌላ እጃቸዉ ደግሞ የከብቶች መመለሻ ዱላ ጨብጠዉ፣ ከሁሉም በላይ ላይ ደግሞ ፋታ የማይሰጠዉን የቤት ዉስጥ ስራ አንድም ቀን ደከመኝና ሰለቸኝ ሳይሉ ያለ ማንም አጋዥ ብቻቸዉን እየማሰኑ ነበር አስተምረዉ እዚህ ያደረሱት። አባቱ ወልዴ ታፈረም ቢሆኑ፣ በደከመ ጉልበታቸዉ ብቻቸዉን ሞፈርና ቀንበር እየተሸከሙ፣ ከደረቀ መሬት ጋር እየታገሉና ከአመት አመት እያመረቱ፣ ለልጃቸዉ የሚሆን በቂ የትምህርት ጊዜን አንድም ቀን ሳያጓድሉ ነዉ አስተምረዉ ዛሬ ላለበት ደረጃ ያበቁት። 
የዚህን ፋይል የፒዲኤፍ (PDF) ቅጅ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!

ለዚህ ነዉ  ታዘበ “ቤተሰቦች እኔ ተምሬ ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ የከፈሉልልኝን መስዕዋትነትና የዋሉልኝን ዉለታ እንኳን እኔ ቀርቶ እግዚያብሔር ራሱ በኔ ቦታ ሆኖ ልክፈለዉ ቢል እንኳ ከፍሎ አይጨርሰዉም።” ሲል በተደጋጋሚ የሚደመጠዉ። በዚህ ሰአት አብርሮ ጎንደር ያደረሰዉም ዋና ምክንያት ይህንኑ መቸም ቢሆን ከፍየ አልጨርሰዉም የሚለዉን የቤተሰቦቹን ዉለታ በመጠኑም ቢሆን ለማቃለል ይረዱኛል ያላቸዉን ሁለት እቅዶቹን ተግባራዊ ለማድረግ ነበር። አንደኛዉና የመጀመሪያዉ ቤተሰቦቼን ያስደስታቸዋል ያላቸዉንና በተለያየ ጊዜና ቦታ እየገዛ ያጠራቀማቸዉን ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን (ልብስ፣ ጫማ፣ የሙዚቃ ማጫዎቻ ቴፕ ወ.ዘ.ተ) እና ለአንዳንድ ነገር ይሆናቸዋል ያለዉን 2,500 ጥሬ የኢትዮጵያ ብር ለቤተሰቦቹ ለማድረስ ሲሆን ሁለተኛዉና ዋነኛዉ ምክንያት ግን የእሱ ተከታይ የሆነችዉን ታናሽ እህቱን አመለወርቅ ወልዴን ከእሱ ጋር ወደ አድስ አበባ ይዞ ለመመለስና ትመህርቷን በቅርብ ሆኖ እየተከታተላትና እራሱ እያገዛት በጥሩ ሁኔታ እንድትማር ያቀደዉን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ነዉ። 

ታዘበ ከተቀመጠበት ቦታ ትንሽ እራቅ ብለዉ ደግሞ አባቱ ወልዴ ታፈረ ከቤተክርስቲያን መልስ ለእርሱዉ እንግድነት መቀበያ ይሆን ዘንድ ያረዱለትን ሙክት በግ፣ በዚሁ እንደ ስጋጃ በተዘረጋ ግቢ ዉስጥ በሚገኝ አንድ መለስተኛ ዛፍ ቅርጫፍ ላይ አንጠልጥለዉ ቆዳዉን በመግፈፍ ላይ ሲሆን የቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ የሆነዉ ክንዴ ወልዴ አባቱን አንዳንድ አስፈላጊ ነገሮችን በማቀበልና በመላላክ እያገዘ ነዉ። የ17 አመት ለግላጋ ወጣት የሆነችዉ አመለወርቅ ወልዴና እናቷ የወርቅዉሀ ታደሰ ደግሞ በተለያዩ የቤት ዉስጥ ስራ ተጠምደዉ ላይና ታች በማለት ላይ ናቸዉ።  ወልዴ ታፈረ የያዙትን ስራ ገታ በማድረግ ብርኩሟ ላይ ተቀምጦ ፀሐይ ወደ ሚሞቀዉ ልጃቸዉ በኩራት እየተመለከቱ፣ አክዬ! እንደዉ ይኽ አድስ አበባ ረብሻ አለ የሚሉት ነገር እንዴት ነበር?  እኛማ እኮ በሰቀቀን ልናልቅ ስንል ነዉ የደረስክልን! በተለይ የናትህንማ አከራረም አታንሳዉ! እንድሁ እህህ! እንዳለች እኮ ነዉ የከረመችዉ! አሉ ማታ ጀምረዉት የነበረዉን ወሬ እንደ አድስ እየቀሰቀሱ። አይ የሷ ነገር!  እንኳን እንድህ ያለ ነገር ሰምታ ዝም ብላስ ቢሆን መጨነቅ አይደል ስራዋ።  አለ ታዘበ እናቱ ወዳሉበት አቅጣጫ በስስት አይን እየተመለከተ። እሱስ ልክ ነህ። እንደዉ እነደሰሞኑ ወሬስ ከሆነ በሷም አይፈረድም።  ወጣቱና ተማሪዉ እንዳለ አልቋል አሉ፣ ከተማዉ በሙሉ በሬሳ ተሞልቷል አሉ፣ እንኳን ወጣቱን ሽማግሌዉንና ሴቱን ሁሉ  እያሰሩ ነዉ አሉ፣ ምን የማይወራ መዓት ነበረ መሰለህ። አሉ ወልዴ ታፈረ የበጉን የዉስጥ ቆዳ በያዙት የቢላዋ ቂጥ ወደ ዉስጥ ገፋ ገፋ እያደርጉ።

ምን እሱማ ሰዉ እንኳን ትንሽ ነገር አግኝቶ ዝም ብሎስ ከመሬት ተነስቶ መአት አዉሪ አይደል! በርግጥ አድስ አበባ ትንሽ ያስፈራ ነበር። አሁንም ገና ዉጥረቱ አልበረደም፣ መንግስት ሰዎችን ኢህአፓ ናችሁ በሚል ሰበብ ያላግባብ በአደባባይ እየረሸነና እያሰረ ነዉ።  አለ እንደ መተከዝ ብሎ።  አባቱ ወልዴ ታፈረም እንደ መተከዝ ካሉ በሗላ፣ አዬ ጉድ! እንደዉ እንዴት? ያለዉ ጊዜ ላይ አደረስን ልጄ! እዚህ ታች ጎንደር ከተማም እኮ ሰዉ እሚባል አልተረፈም አሉ እኮ። እዛማ ደግሞ ይብስ ብለዉ የገደሉት ሰዉ እሬሳ እንኳ እንዳይነሳና እንዳይለቀስ ይከለክላሉ ነዉ እኮ እሚባለዉ። አሉ አይገርምህም በሚል አስተያዬት ልጃቸዉን እየተመለከቱ። ሁለቱም በጋራ ትንሽ በዝምታ ከቆዘሙ በሗላ፣ አድስ አበባም እኮ ቢሆን እደዚህ ያደርጋሉ። አለ ታዘበ በቀዘቀዘ ድምጽ።  ወቸ ጉድ! አሁንማ እዚህ እኛስ ድረስ እየመጡ መግደል ጀምረዉ የለም እንዴ። አሁን በቀደም እለት አይደል እንዴ ከከተማ አምልጦ የመጣ የመንግስት ጠላት ነዉ ብለዉ እንዴት ያለዉን ለግላጋ ወጣት እዚህ ታች ካለዉ ከናንተ ከተማሪ ቤቱ በር ላይ በጠራራ ፀሀይ የደፉት። አሉ ወልዴ ታፈረ አቁመዉት የነበረዉን ስራቸዉን እንደገና ለመጀመር እየተዘጋጁ። ታዘበ ድንጋጤ ባዘለ የድመፅ ቃና፣ እነማናቸዉ የገደሉት? አለ አባቱን በአትኩሮት እየተመለከተና ለመስማት እየተቻኮለ። ታዘበ ወልዴ ትንሽ እንደማመንታት ካሉ በሗላ፣ ከከተማ እያመለጡ የሚደበቁ  ኢአፓ ነዉ ምናምን ያልካቸዉን ሰዎች እንዲሰልሉ የታዘዙ የመንግስት ሰዎች ናቸዉ ነዉ የሚሉት። አሉ እኔ ምኑን አዉቄዉ ልጄ በሚል አስተያየት። እንዴ አለ! ታዘበ ሳይታወቀዉ እንደመጮህ እያለ። እንዴ! የኛዉ ቀበሌ ሰዎች ናቸዉ ወይስ ከታች ከከተማ የመጡ? አለ ይበልጥ ድንጋጤ እየተሰማዉ። በዚህ ጊዜ አባቱ ወልዴ ታፈረ፣ ርቀዉ ቆመዉ ከነበረበት ቦታ ወደ ልጃቸዉ ቀረብ አሉና ፊትለፊቱ በሁለት እግራቸዉ ቁጢጥ ብለዉ በመቀመጥ፣ እህ! ገዳዮቹማ ከሌላ ቦታ በመንግስት የተላኩ ናቸዉ ነዉ የሚባለዉ።ይኸ ማነዉ የሚባለዉ ጎንደር ያለዉ ዋናዉ የመንግስቱ ሹም፣ አዎ መላኩ ተፈራ በሚባለዉ፣ አሉ ወልዴ ታፈረ እንደመገረም እያሉ። ጠቁሞ ያስገደለዉ ግን ይኸ የኛዉ ቀበሌ ሊቀመንበር የሆነዉ አስቻለዉ ነዉ ይባላል። አሉ በአገጫቸዉ በቅርብ እርቀት ወደሚገኘዉ ባለሳር ክዳን ጎጆ ቤት እየጠቆሙት። ታዘበ ያሳዝናል በሚል አይነት ጭንቅላቱን በማወዛወዝ ወደ ቤቱ አቅጣጫ አሻግሮ እየተመለከተ መልስ ሳይሰጥ ዝም አለ። ወልዴ ታፈረ ትንሽ በዝመታ ከቆዩ በሗላ፣ ኩራትን በሚያሳብቅ የለሆሳስ ድምፅ  ወደ ልጃቸዉ ጆሮ ጠጋ ብለዉ፣ እንዴት ያለ የተበላሸ ሰዉ ሆኗል መሰለህ። ይኸዉ የቀበሌዉ ሰዉ ሁሉ ፈርቶት ሊሞት ነዉ። እኔ አባትህ ወልዴ ታፈረ ብቻ ነኝ ምን አባቱ ያመጣል ብዬ አላጎበድድም ያልኩት። አሉና እንደመጀነን ብለዉ ዝም አሉ። 

ብዙም ሳይቆይ እ!እ! የሚል የማቃሰት ድምጽና ወይኔ ልጄን! ወይኔ ልጄን! የሚል ጩኸት በሰላማዊ ጸጥታ ተሞልቶ የነበረዉን የግቢዉን አየር ከመቅጽበት ከዳር ዳር ደርሶ አደፈረሰዉ። ወይኔ ልጄን! ወይኔ ልጄን! አሉ ወልዴ ታፈረ አሁንም በድጋሜ ጉልበታቸዉ ላይ የተደፋዉን በደም የራሰ  የልጃቸዉን ጭንቅላት ካዘነበለበት ቀና ለማድረግና ለማየት እየሞከሩ። ይህን ተከትሎ እሪ! እሪ! ያገር ያለህ! የመንግስት ያለህ! ያገር ያለህ! የሚለዉ የወርቅዉሀ ታደሰ ጩኸትና የሌሎች የበረካታ ሰዎች ኡኡታና ዋይታ ግቢዉን በአንድ ጊዜ የተዋጣለት የለቅሶ አደባባይ አስመሰለዉ። እመቱ የወርቅዉሀ ታደሰ የሟች ልጃቸዉን ጭንቅላት ከባለቤታቸዉ ጉልበት ላይ በመዉሰድ ደረታቸዉ ላይ ሸጉጠዉ ነፍሳቸዉን እስኪስቱ ድረስ በኡኡታና በእሪታ እየተናጡ ተፈራፈሩ። አባት ወልዴ ታፈረ የሚይዙትንና የሚጨብጡትን አጥተዉ አንደ ወደ ግራ ሌላ ግዜ ወዴ ቀኝ፣ አንደ ወደ ላይ ሌላ ጊዜ ወዴ ታች ተሯሯጡ፣ ወጡ ወረዱ። ዳሩ ግን የማናቸዉም ልፋትና ድካም፣ የትኛዉም ዋይታና ኡኡታ ግን ግንባሩን በጥይት ተመትቶ በደም ጎርፍ የሚታጠበዉን የልጃቸዉ የታዘበ ወልዴን አንጀት አራርርቶ ከጀመረዉ የሞት መንገድ  ሊያስቀረዉ አልቻለም።

***
 ጎንደር-ጋይንት
1970፣ ሐሙስ፣ ከምሽቱ 3፡50
አንድ መለስተኛ ባለ ሳር ክዳን የገጠር ጎጆ ቤት ውስጥ አባት፣ እናትና አንድ ወንድ ልጃቸዉ ዘዎትር እንደሚያደርጉት ሁሉ የምድጃዉን እሳት ዙሪያዉን ከበዉ ተቀምጠዋል። እናት ቶሎ ቶሎ እየጠፋ የሚያስቸግራቸዉን እሳት እንደገና ለማቀጣጠል ከጎናቸዉ ወደሚገኘዉ የጭራሮ ማገዶ እንጨት እጆቻቸዉን በደመነፍስ በአየር ላይ እየላኩ በመዉሰድ እሳቱን እንደገና ለማቀጣጠል እየጣሩ ነዉ። አባት በሰፌድ የቀረበላቸዉን ቆሎ በጨለማዉ መሀል በሻካራ እጃቸዉ እየዳበሱ በሀሳብ ተዉጠዉ ያንቀራጫሉ። ለቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ የሆነዉ የ12 አመት ልጃቸዉ ክንዴ ወልዴ ደግሞ መደብ ላይ ተኮርምታ የተኛችዉን ታላቅ እህቱን በጨረፍታ እየተመለከተ ከምድጃዉ ዳር የተከመረዉን አመድ በትናንሽ ጣቶቹ እያንከላወሰ ይተክዛል። በቤቱ ዉስጥ እመት የወርቅዉሀ ታደሰ ከሚያንኮሻኩሹት የጭራሮ እንጨትና በተደጋጋሚ ከሚያሰሙት እፍ! እፍ! የሚል ድምጽ ሌላ ምንም አይነት ነፍስ ያለዉ ፍጥረት በቤቱ ዉስጥ የሌለ በሚሰል አኳሗን ከባድ ዝምታ ተዉጦታል።

ከአንድ ወር በፊት በአብዮታዊ ሀይሎች ኢህአፓ ነዉ በሚል ምክንያት በጠራራ ፀሐይ የገዛ ቤቱ ደጃፍ ላይ የተገደለዉን የልጃቸዉ ታዘበ ወልዴን ድንገተኛ ሞት ተከትሎ ነበር ዝምታ እንድህ ከነዘር ማንዝሩ ተጠራርቶ እዚህ ቤት ዉስጥ እንዲከትም ያደረገዉ። አባትና እናት በስንት ድካም አስተምረዉ ለወግ ለማዕረግ ያበቁት የልጃቸዉን ፍሬ ማጣጣም ይቅርና ገና አይኑን እንኳን አይተዉ ሳይጠግቡት እንደቀልድ የገዛ በራፋቸዉ ላይ መሞቱን  በአይናቸዉ በብረቱ ቢያዩም አናምንም በማለት እንደወትሮዉ ሁሉ በር በሩን በናፍቆት እያዩ ተስፋ የጣሉበት ልጃቸዉ ተመልሶ ይመጣ እንደሁ ለብዙ ቀናት በሀዘን ጅራፍ እየተገረፉና በሰቀቀን እየማቀቁ ጠብቀዉታል። የሆነዉ ነገር ሁሉ በእዉናቸዉ እንጅ በህልማቸዉ አለመሆኑን ሲያረጋግጡ ደግሞ እህህ! እያሉ ከማንባት በቀር አቅም አልነበራቸዉምና እንድሁ እህህ! እያሉ የማያባራ የእምባ መስዕዋትን ለሟች ልጃቸዉ ማቅረብ ከጀመሩ እነሆ አንድ ወር አለፋቸዉ።

እናቱ የወርቅዉሀ ታደሰ በተለይ እሳቸዉ እራሳቸዉ በእንባ ጎርፍ ታጥበዉ ሊያልቁ ነዉ እስኪባሉ ድረስ ያለማቋረጥ ሌትና ቀን አንብተዉለታል-ለሟች ልጃቸዉ ታዘበ ወልዴ። የሟች ተከታይ የሆነችዉ ታናሽ እህቱ አመለወርቅ ወልዴም ብትሆን እናቷ በሀዘን ብዛት አደጋ ላይ እንዳይወድቁባት በመፍራትና የቤተሰቡን ሆድ ላለማባባት በሰዉ ፊት ሀዘን ያልገባት ብርቱ መስላ ብትታይም፣ በድብቅ እንደ አይን ብሌኗ ትሳሳለት ለነበረዉ ወንድሟ ያለማቋረጥ እንባ ሳይሆን ደም አንብታለታለች። አባቱ ወልዴ ታፈረና ታናሽ ወንድሙ ክንዴ ወልዴ ግን ሀዘን እንደ መሮ ነጋ ጠባ ቢቆረቁራቸዉም፣ በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት ቀናቶች በስተቀር የእንባ ከረጢታቸዉን ሊፈቱለት አልፈቀዱም! ከዚያ ይልቅ ከአንድም ሺ ጊዜ ታግለዉ እየመለሱ ሆዳቸዉ ዉስጥ ቀብረዉ አስቀርተዉታል። እምባና ቁጭታቸዉን! 

እመት የወርቅዉሀ ታደሰ ድንገት የሚቆሰቁሱትን ጭራሮ ገታ በማድረግ፣ አዬ አንተ መድሐንአለም! እዉነት የለህማ! እዉነት በድሀ ጎኔ አልዘከርኩህማ! አዬ! አዬ! በሚል ሸካራ ድምጽ ቤቱን ሞልቶት የነበረዉን ጸጥታ አደፈረሱት። ባለቤታቸዉ ወልዴ ታፈረም ገብተዉበት ከነበረዉ የሀሳብ አለም በቅጽበት ብንን አሉና አካባቢያቸዉን ትንሽ ቃኘት መባድረግ፣ ኤድያ! ሀዘኔን አብዛልኝ ያልነዉ ይመስል በየአመቱ የሀዘንና የመከራ ሸክም ከመከመር በቀር የሱ ዝክር ምን ጠቀመን? አሉ ብስጭት ባለ ድምጽ። እመት የወርቅዉሀ  ድንግጥ ብለዉ ባለቤታቸዉን በዝመታ ገረመሙዋቸዉ። በሀሳብ ተዉጠዉ እዚህ እና እዛ እየተንክላወሱ ስለነበር ለራሳቸዉና ለመድሐኒአለም ብቻ በለሆሳስ የአንሾካሾኩ እንጅ እንድህ ጮኸዉ ሌሎቹ እስኪሰሙዋቸዉ ድረስ የተናገሩ አልመሰላቸዉም ነበር። ሁሉም በዝምታ ዉስጥ ሆነዉ ትንሽ ከቆዩ በሗላ እመት የወርቅዉሀ ቀጠል አደረጉና! አይ! እይ! እረ እንደዉ አሁንስ በዛ! እረ በዛ! ከቶ የዚህን ያህል ምን በደልነዉ? እንደ ሰዉ ታቦት አልዘረፍን፣ ሰንበትን አልሻርን፣ ድምበር አልገፋን ወይ እንደሰዎቹ ቀምተን አልበላን። እራሱ የሰጠንን ጉሮሮ ለመድፈን ሌት ተቀን ደፋ ቀና ከማለት ሌላ ምን በደልነዉ? አሉና ትንሽ ዝም ካሉ በሗላ “ወይ ምናለ ይኸን ሁሉ መከራ በቁሜ ከሚያሸክመኝ ክልትዉ አድርጎ ቢገላግለኝ!” አሉ እንደልማዳቸዉ በእንባ ብዛት የተዳከሙ አይኖቻቸዉን በቀኝ እጃቸዉ መዳፍ እሸት እሸት በማድረግ ለማያባራዉ እንባቸዉ መንገድ እየጠረጉ። 

እመት የወርቅዉሀ ታደሰ አንድ ጊዜ ማልቀስ ከጀመሩ በዋዛ እንደማያቆሙ ባለቤታቸዉ ወልዴ ታፈረ ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ።  እንደ ሌላ ጊዜዉ ቢሆን ኖሮ ሚስታቸዉ እንድህ ሆድ ብሷቸዉ ማልቀስ ሲጀምሩ፤  ተይ እንጅ የወርቅ! እንደሱ አትሁኝ! ሁል ጊዜ  እኮ ደስታ የለም። እግዚያብሔር የሚወደዉን ይፈትናል! የሚወደዉን ያደርጋል! ደግሞስ ምን ጎደለን? ይችን አመጣህ ብሎ ማማረር ደግ አይደለም! ተይ አታልቅሽ! የባሰ አታምጣ ነዉ እንጂ እሚባለዉ! ምንድን ነዉ ማልቀስ! በማለት ይገጽጿቸዉና ያጽናኑዋቸዉ ነበር። ዛሬ ግን ከዚህ ይልቅ በቀኝ እግራቸዉ መዳፍ የረገጡትን መሬት በትካዜ ቃና እየደበደቡ፣ ምነዉ ባገኘሁህ በሚል አስተያየት ጣራ ጣራዉን አንጋጠዉ እየተመለከቱ  ዝም አሉዋቸዉ። በዚህ መሀል ብቸኛ ሴት ልጃቸዉ  አመለወርቅ ወልዴ ምሬትና ሳግ በተቀላቀለበት አንደበት እረ! ተይኝ ይኸን ለቅሶ እማዬ! እረ ተይኝ! እኔስ እንደዉ ላንቺ ስል  ወዴት ሀገር ልሂድልሽ? እንደዉ ምን ዉስጥ ልግባልሽ? በሚሉ የተለመዱ ቃላቶቿ የእናቷን ለቅሶ ለመግታት ተጣጣራች። እናት ልጃቸዉን ቀና ብለዉ ካዩ በሁዋላ፣ ጎድጓዳ ስሀን የመሰለ ጉንጫቸዉ ላይ የሚወርደዉን እንባ ባይበሉባቸዉ እየጠራረጉ፣ እሺ አላለቅስም፣ ላልቅስስ ብል በምን እድሌ! እምባዬን በክፉ ቀን ጨርሸዉ አሉና ዝም አሉ። ሁሉም በዝምታ ለትንሽ ጊዜ ከቆዩ በሗላ፣ ደግሞ በላይ እንደገዳይ ቆይ ዋጋህን እሰጥሀለሁ ይበለኝ! ይህ ሽንታም! አያዉቅም እንደ እንዴት አበራየዉ እንደነበር:: ዛሬ እሱ ባለ ጊዜ ሆኖ የመንግስትን ብረት ስላነገተ የምፈራዉ መሰለዉ እንዴ? አልጫ! የሚለዉ የወልዴ ታፈረ በወኔ የተሞላ ድምጽ ቤቱን  እንደገና ገብቶበት ከነበረዉ አስፈሪ ፀጥታ ቀሰቀሰዉ። 

ወልዴ ታፈረ በማለዳ ተነስተዉ ሞፈራቸዉን እራሳቸዉ ቀንበራቸዉን ደግሞ ለክንዴ አሸክመዉ በጧት እርሻቸዉ ላይ ለመጥመድ ጥንድ በሬወቻቸዉን እየነዱ ሲሄዱ ሳለ ነበር ከቀበሌቸዉ ሊቀመንበር አስቻለዉ ታከለ ጋር መንገድ ላይ የተገናኙት። ወልዴ ታፈረ በቅርቡ የሞተዉን ልጃቸዉን ኢህአፓ ነዉ በሚል ጠቁሞ ያስገደለዉ እሱ ነዉ ብለዉ ስላመኑ አስቻለዉን አይጠሉ አጠላል ጠልተዉታል። አስቻለዉም ቢሆን ይህን ጠንቅቆ ስለሚያዉቅ ብዙ ጊዜ ከሳቸዉ ከመጠበቅ ይልቅ እሱ እየገፋ ነዉ ሰላምታ የሚሰጣቸዉ። ዛሬም እንደ ሌላዉ ጊዜ፣ የቀዳሚነቱን ሚና እራሱ በመዉሰድ ነበር እንደምን አደሩ ጋሽ ወልዴ? በሚል ቀዝቃዛ ድመጽ ሰላመታ ያቀረበላቸዉ። ወለዴ ታፈረ ግን ደግሞ አለማፈርህ! በሚል አይነት ፊታቸዉን ቅጭም አድርገዉ መልስ ሳይሰጡት አልፈዉት ሄዱ። አስቻለዉ ግን ያልገባዉ በሚመስል አኳሗን ፈጠን አለና ጋሽ ወልዴ የገበሬ ማህበሩ ስብሰባ ላይ ለምንድነዉ የማይገኙት! እኔ አኮ ርምጃ መዉሰድ አቅቶኝ አይደለም። ከዛሬ ነገ ያሻሽሉ ይሆናል በሚል ነዉ እንጅ። አለ አሁንም ቢሆን የፈለኩትን ከማድረግ የሚከለክለኝ የለም የሚል ቅላጼ ባለዉ አነጋገር። 

በዚህ ሰዓት የወልዴ ታፈረ ትግስት አፍንጫቸዉ ላይ ደረሰ። ድንገት ወደ አስቻለዉ ዞር በማለት ከዘራቸዉን አፍንጫዉ ስር  እየጠቆሙ  እ! ጧሪ ቀባሪዬ የነበረዉን አንድያ ልጄን ቀማችሁኛ፣ እነ ጅቦ! የተረፉትን እንኳ በደካማ ጉልበት አርሸ እንዳላበላ ነዉ ገበሬ ማህበር ምንትስ እያላችሁ ስራ እምታስፈቱኝ? እ! ነዉ እነሱንም ልትበሉአቸዉ አሰባችሗል? ንገረኝ እንጅ! አሉ አስቻለዉ አፍንጫ ስር የዘረጉትን ከዘራ ይበልጥ ወደ አፍንጫዉ እያስጠጉ።  እንዴ! ምንድነዉ የሚሉት አባ ወልዴ? አለ አስቻለዉ ግራ የተጋባዉ በሚመስል ድምጽ። ወልዴ ታፈረ ግን ይበልጥ በንደት እየተንዘረዘሩ፣  እንድህ  ቆማችሁ ሲያዩዋቸሁ ሰዉ ትመስላላችሁ! አረመኔ አዉሬዎች! ሂድና ንገራቸዉ ከአዉሬ ጋር እኔ ማህበር የለኝም ብሏል ወልዴ ታፈረ በላቸዉ አሉና መንገዳቸዉን ለመቀጠል ፊታቸዉን አዙረዉ መንቀሳቀስ ጀምሩ። በዚህ ጊዜ ነበር አስቻለዉ በተራዉ በንዴት ጦፎ፣ ምን አልክ? አንተ ግተት ሽማግሌ! ያልካትን እንዳትረሳት! እረ! እረ! እንዴት ጠግበሀል እባክህ?  ቆይ ጠብቀኝ ዋጋህን ነዉ የሚሰጥህ፣ አለ ከሳቸዉ ምንም መልስ ሳይጠብቅ ወደሚሄድበት አቅጠጫ ዞሮ መንገድ እየጀመረ። ወልዴ  ታፈረ ጀምረዉት የነረዉን መንገድ ገታ አደረጉና፣ አየ ሽንቶ! የምፈራህ መሰልህ እንዴ? አንት አተላ! አሁንስ አለሁልህ አይደል! ለምን አትመጣም? ጅብ ከማያዉቁት አገር ሄዶ ምን አንጥፉልኝ አለ አሉ። አናዉቅህም እንዴ አንት እበት! መጄመሪያ እስኪ እኩዮችህን አሸንፍ። ጀግንነት ማለት ማቃጠር ነዉ አሉህ እንዴ? አሉ በቀኝ እጃቸዉ የያዙትን ዱላ ለመሰንዘር እያመቻቹ። እኮ እሽ እሱን ስትጠየቅ ትመልሳለህ። አሁን ዝም ብለህ መንገድህን ቀጥል! ከእንዳንተ አይነት ዛዛታም ሽማግሌ ጋር ዱላ ገጥሜ የሰዉ መሳቂያ መሆን አልፈልግም አለና አስቻለዉ በቆሙት ትቷቸዉ እየተጣደፈ ሄደ።    

ይህን የጧት ገጠመኛቸዉን በማስታዎስ ነበር ወልዴ ታፈረ “ደግሞ በላይ እንደገዳይ ቆይ ዋጋህን እሰጥሀለሁ ይበለኝ!” ሲሉ የተብሰለሰሉት። አባቱ ጋር አብሮ የነበረዉና ይህንኑ ትይንት በአንክሮ ሲመለከት የነበረዉ ትንሹ ክንዴ ለእናቱ የወርቅዉሀ ታደሰ አንድም ሳያስቀር ተርኮላቸዉ ነበርና ስጋትን በሚያስተጋባ ድምጽ፣ እረ! እባክህ አንተ ሰዉዬ ከማይነካኩት ሰዉ ጋር አትነካካብኝ። ምንስ ቢሆን እኮ እሱ ዛሬ ባለጊዜ ነዉ። ምናለ እስቲ አልመቸኝ ብሎ ነዉ እንጅ እመጣለሁ ብትለዉ አሉ። አቋርጠዉት የነበረዉን ለቅሶ እንደገና ለመጀመር እየቃጣቸዉ። ወልዴ ታፈረ ግን የሚስታቸዉን ተግጻጽ ያልሰሙ በመምሰል፣ ዳሩ እሱ ምን ያድርግ ሰዉ አጣብኛ። አሉ አምቀዉ ይዘዉት የነበረዉን አየር በሀይል ወደ ዉጭ እየተነፈሱ። 

ቤቱ አሁንም በድጋሜ በጸጥታ ተዉጦ ለትንሽ ጊዜ ከቆየ በሗላ፣ እንደት አመሻችሁ እዚህ ቤት? የሚል ከዉጭ የመጣ ድምጽ የሁሉም የቤተሰቡ አባላት ጆሮ ላይ አስተጋባ።  ከመቅጽበት ሁሉም በድንጋጤ ክዉ ብለዉ ፊታቸዉን ድምጹ ወደ መጣበት አቅጣጫ በማዞር ለማዳመጥ ጆሯቸዉን አቁመዉ ጸጥ አሉ። ቤቶች! አለ አሁንም የቅድሙን የሚመስል ድምፅ በድጋሜ። በዚህ ሰአት እመት የወርቅዉሀ ታደሰ ከድንጋጣቸዉ ትንሽ መለስ አሉና፣ አቤት! ማነዉ? አሉ። እኔ ታሪኩ ነኝ እማማ። አለ ዉጭ ቆሞ ሲጣራ የነበረዉ ሰዉ። ይሄኔ ለባላቸዉን ከተቀመጡበት እንዳይንቀሳቀሱ በአይናቸዉ ምልክት እየሰጡ ማን ታሪኩ? የኛ ታሪኩ አሉ የቀበሌያቸዉ ምክትል ሊቀመንበር የሆነዉ ታሪኩ እንደሆነ እርግጠኛ እየሆኑ። አዎ እማማ ደህና አመሹ አለ ሰዉዬዉ። እስቲ ቆይ መጣሁ! ምነዉ በጨለማ ደህና አይደላቸሁም እንዴ? አሉ እመት የወርቅዉሀ ታደሰ  የቤታቸዉን በር እየከፈቱ። 

እመት የወርቅዉሀ በራቸዉ ላይ በጨለማ ለቆሙት ሁለት ሰዎች ሰላምታ እየሰጡ እንዴት አመሻችሁ ልጆቼ? ምነዉ ከመሸ? አሉ ከታሪኩ ጋር አብሮት የቆመዉን ሰዉ ማንነት በጨለማዉ መሀል ለመለየት እየመከሩ። ታሪኩ ፈጠን አለና አይ ድንገት ከመሸ ሆኖ ነዉ የሰማነዉ እማማ። አባ ወልዴን ፈልገን ነበር አለ።  እመት የወርቅዉሀ በድንጋጤ ክዉ ብለዉ ምነዉ? ለምን? በዚህ ጨለማ  ሲነጋ አይደርስም ነበር እንዴ? አሉ።  ታሪኩ ምን መልስ መስጠት እናዳለበት እያሰላሰለ ባለበት ቅጽበት፣ ቤት ዉስጥ ተቀምጠዉ  የነበሩት  ወልዴ  ታፈረ ሁለቱን ልጆቻቸዉን ከሗላቸዉ አስከትለዉ እንዴት አመሻችሁ ልጆቼ? በማለት እነ ታሪኩን ተቀላቀሉ። እንደምን አመሹ አባ ወልዴ? ከቀበሌ ነዉ ተልከን የመጣነዉ አለ ታሪኩ አሁንም ፈጠን እያለ። ምነዉ በደህና አሉ ወልደ ታፈረ። አዎ በደህና ነዉ አባ ወልዴ እኛ ጋር ቀበሌ እንድናሳድረዎት ተልከን ነዉ  የመጣነዉ አለ ታሪኩ እንደመሽኮርመም ብሎ። ምነዉ ለምን? ቤቱ ምን አለዉ? አሉ አሁንም እመት የወርቅዉሀ ምን እያለ እንደሁ እንዳልገባቸዉ በሚያሳብቅ አኳሗሗን። አሀ! ምነዉ? ሲነጋስ ቢሆን ና ብባል አልመጣም ነበርና ነዉ እንድህ እንደሸፍታ በምሽት አደን የመጣችሁት? ነዉ ወይስ ፈርቸ አገር ጥዬ እንዳልጠፋ? አሉ ወልዴ ታፈረ እኛ ጋር ቀበሌ እንድናሳድረዎት ማለት ታስረዉ ማደር አለብዎት ማለት እንደሁ ስለገባቸዉ።

እረ1 እንደዛ አይደለም አባ ወልዴ። መልክቱስ ቀን ነበር አሉ የተላከብን፣ መልክተኛዉ ረስቶት ከመሸ ስለነገረን ነዉ እንጅ። አለ ታሪኩ በድጋሜ እየተሽኮረመመ። አሁንም ነገሩ ያልገባቸዉ እመት የወርቅዉሀ ታደሰ፣ እረ ምንድነዉ ጉዱ? ምናለ ብትነግሩኝ አሉ፣ አንድ ጊዜ እነ ታሪኩን ሌላ ጊዜ ደግሞ  ሽማግሌ ባላቸዉን በተማጽኖ እየተመለከቱ። ምንም አይደል የወርቅ! ቀበሌ ታሰረህ ማደር አለብህ ነዉ የሚሉኝ አሉ ወልዴ ታፈረ። ወድያዉ ምንም መልስ ሳይጠብቁ፣ ክንዴ እስኪ ከዘራዬን አቀብለኝ አሉ የሚስታቸዉን ፊት ላለማየት አይናቸዉን ወደ ሌላ አቅጣጫ እያዞሩ። ምነዉ? ምነዉ? ልጆቼ! እረ እሪ! እረ የነፍስ! እረ እባካችሁ ነገ ጧት ዉሰዱት። አይኑም እኮ በጨለማ አያይለት። ታሪኩ! የኔ ልጅ! እረ የነፍስ! አሉ እመት የወርቅዉሀ ታደሰ የሚይዙ የሚጨብጡትን አጥተዉ። አይዞዎት እማማ ምንም አይሆኑ። እኛስ ብንሆን ምን እናድርግ ብለዉ ነዉ? ታዘን እኮ ነዉ። ባይሆን ቀስ አድርገን እናደርሳቸዋለን። አለ  ታሪኩ ወደፊት ለመሄድ እየተዘጋጀ። እመት የወርቅዉሀ ታደሰ መንገድ ለመዝጋት በሚመስል አኳሗሗን ከታሪኩ ፊት ቀደም አሉና፣ እረ አሪ! አረ የነፍስ! እረ ነገ ጧት ዉሰዱዋቸዉ አሉ በድጋሜ እየተርበተበቱ። ይሄኔ ወልዴ ታፈረ ቆጣ አሉና እህ! የወርቅ ምን ሆነሻል? ለአንድ ቀን ታስሬ ባድር ምን እንዳልሆን ነዉ? ይልቅ ልጆቹን ይዘሽ ግቢና በሩን ዘግታችሁ ተኙ አሉ።  

በዚህ ጊዜ ድምጹን እስካሁን አጥፍቶ የነበረዉ ሁለተኛዉ ሰዉ፣ እንደዛ ይሻላል እማማ አለ ወልዴ ታፈረን እንቀሳቀስ በሚል ሁኔታ እየተመለከተ። እመት የወርቅዉሀ የሰዉየዉ መልክ ብቻ ሳይሆን ድምፁም አድስ እንደሆነ በተገነዘቡ ጊዜ ይበልጥ እየቀፈፋቸዉ፣ እረ እዝጎ! እረ የነፍስ አሉ አሁንም መንገድ የጀመሩትን ሶስቱን ሰዎች ከሗላ እየተከተሉ። ወልዴ ታፈረ ጀምረዉት የነበረዉን መንገድ ድንገት ገታ አደረጉና፣ እንዴ! የወርቅ የምን ዋይታ ማብዛት ነዉ! ግቢ እኮ አልኩሽ ባይሆን ካልመጣሁ ነገ በጧት መጥታችሁ ትጠይቁኛላችሁ አሉና መልስ ሳይጠብቁ በቆሙበት ትተዋቸዉ ሄዱ።  እመት የወርቅዉሀ ታደሰ የሚያደርጉትን አጥተዉ፣ እንዴት ሽማግሌ በቤቱ ማደሪያ ይጣ? እንዴት ሰዉ ባገሩ መኖሪያ ይጣ? እረ የምን መአት ነዉ የወረደብን? እረ! እዝጎ! እረ! እዝጎ! አሉ ሶስቱን ሰዎች በአይናቸዉ እየሸኙ። እንደዉ እኔስ እሪ ልበልና አገር ጉደን ይስማልኝ እንዴ አሉ እመት የወርቅዉሀ ለራሳቸዉ በሚሰማ ድምጽ ከቆሙበት ሳይንቀሳቀሱ። አሁን እሪ ማለቱ ምን ይጠቅማል ባይሆን የነገዉን ሁኔታ አይተን የሆነ ነገር ብናደርግ ይሻላል እንጂ አለች አመለወርቅ ጉንጯ ላይ ያለከልካይ የሚወርደዉን እንባ እንዳይታይባት በመዳፏ እየጠረገችና እንደ ሀዉልት ተገትረዉ የቆሙ እናቷን ደግፋ ወደ ቤት ይዛቸዉ ለመግባት እየሞከረች። እዝጎ! እዝጎ! ይላሉ እመት የወርቅዉሁ ታደሰ የልጃቸዉን ትክሻ ተመርኩዘዉ በደመነፍስ እየተንቀሳቀሱ። በዚህ መሀል ሁለቱም ተዛዝለዉ የቤታቸዉ መግቢያ በር አጠገብ እንደደረሱ ከቅርብ እርቀት የመጣ የተኩስ ድምጽ ድንገት የሁለቱም ጆሮ ላይ ደርሶ አምባረቀ። እመት የወርቅዉሀ ታደሰ ተጭኗቸዉ የነበረዉን ድካም አሸንፈዉ፣ ተደግፈዉት የነበረዉን የልጃቸዉን ትክሻ ለቀዉ በሀይል ወደ መዉጫዉ በር እየሮጡ እሪሪሪሪሪ! ገደሉት! የአገር ያለህ፣ የመንግስት ያለህ፣ የድሀ ያለህ! እሪሪሪሪ! ገደሉት! ገደሉት! በማለት ሚያሰሙት የጣር ድምጽ  በብርሃን ፍጥነት እየተፈተለከ እያንዳንዱ ደሳሳ ጎጆ ቤት በር ላይ ደርሶ በማንኳኳት፣ የሰቆቃቸዉን ልክ፣ የሰቀቀናቸዉን ብዛት፣ የስቃያቸዉን መጠን… የሀዘናቸዉን ስፋት… እሪሪሪረሪ! ገደሉት! ያገር ያለህ! የመንግስት ያለህ! ገደሉት! እያለ አስተጋባላቸዉ።

ማስታወሻ፡ ይህ ታሪክ በ1969 መጨረሻዎቹ አካባቢ ጎንደር- ጋይንት ዉስጥ ይኖር በነበረ አንድ ቤተሰብ ላይ የደረሰ አሳዛኝ ታሪከ ሲሆን በታሪኩ ዉስጥ ለተጠቀሱት ሰዎች ደህንነት ሲባል በታሪኩ ዉስጥ የተገለጹት ስሞች የብዕር ስሞች እንጂ ትክክለኛ የባለታሪኮቹ ስሞች እንዳልሆኑ ለመግለጽ እንወዳለን። እመት የወርቅዉሀ ታደሰ የባላቸዉን ሞት ተከትለዉ ብዙም ሳይቆዩ ከሞቱ በሗላ የቤተሰቡ ብቸኛ ሴት ልጅ የነበረችዉ አመለወርቅ ወልዴ በወቅቱ ደርግን ለመጣል ይደረግ የነበረዉን ትግል በመቀላል እስከ 1978 ድረስ ስትታገል ቆይታ 1979 መጀመሪያ አካባቢ በተካሄዴ አዉደ-ዉጊያ ላይ በዉጊያ ላይ ሳለች ከጠላት ወገን በተተኮሰ ጥይት ተመትታ ህይዎቷ ሊያልፍ ችሏል።  በአሁኑ ሰዓት ከዚህ የቤተሰብ አባላት ዉስጥ በህይዎት የሚገኘዉ የቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ የሆነዉ ክንዴ ወልዴ ሲሆን ከብዙ ዉጣ ዉረድና ድካም በሗላ አሜሪካን አገር ለመግባት የቻለ ሲሆን በአሁኑ ሰአትም እዛዉ አሜሪካን አገር ዉስጥ የራሱን ህይዎት መስርቶ በመኖር ላይ ሲሆን የአንድ ወንድና የሁለት ሴት ልጆች አባት ለመሆን በቅቷል። 






------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

1 comment:

  1. The Wizard of Oz Casino Resort Review and Bonus Codes
    Casino Promotions. One of the most well known in the online gaming industry, The Wizard 익산 출장안마 of Oz 제주도 출장샵 is 경기도 출장마사지 a 영주 출장샵 highly respected 충청북도 출장샵 casino that has been around since 1996 and has

    ReplyDelete