Sunday, May 6, 2012

አንድ ሀገር አንድ ህዝብ ጦማር አፈና ተደረገባት!

አየር ላይ በዋለች 5 ቀን ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ብቻ ከ450 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ከተለያየ ሀገር የጎበኟትና የተለያዬ ባህል፣ ቋንቋና እምነት ባላቸዉ አምስት ግለሰቦች የጋራ ትብብር  የተመሰረተችዉ፣ “አንድ ሀገር አንድ ህዝብ” ጦማር በዚህ ሰአት ኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉ ወዳጆጃችን እንዳይከታተሏት አፈና እንደተደረገባት ተገልጾልናል። ጦማራችን በዘርፈ-ብዙ ሀገራዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ግለሰባዊ ምልከታዎች ማቅረብ ጀምራ የነበረች ሲሆን ከነዚህ በተጨማሪ በሌሎች በርካታ ኪነጥበባዊ፣ ሐይማኖታዊ፣ ፍልስፍናዊ፣ እና ስነ-ጽሁፋዊ ስራዎችና እሳቤዎችም ተጨማሪ ግንዛቤዎችን ለማስጨበጥ ደፍ ቀና በማለት ላይ ባለችበት በዚህ ሰዓት የኢንሳ (INSA) ሰለባ መሆኗ ቢያሳዝነንም እዉነትን በማፈን አልያም ወደ ዉሸት bመቀየር መደበቅ/ማጥፋት/ እንደማይቻል ለአፈኞቻችን ለመግለጽ እንዎዳለን። 


ሕዝብ መንግስት ከሚደሰኩረዉ ተልካሻ የፖለቲካ ፕሮፓካንዳ ዉጭ ሌላ ምንም ነገር እንዳይሰማና ምንም አይነት አማራጭ እንዳይኖረዉ ማድረግ ትዉልድን በጦር መሳሪያ አሰልፎ በጅምላ ከመግደል በከፋ መልኩ ሀገርን የመግደል ሴራ ነዉ። መሳሪያ አንሰቶ ማጥፋት የሚቻለዉ የሰዉን አካላዊ ስጋ እንጂ እምነቱንና ያነገበዉን አላማ ግን ፈጽሞ ሊሆን አይቻልም። ለዚህም ነዉ ትናንት ላመኑበትና ለተሰለፉበት አላማ ግንባራቸዉን ለጥይት ሰጥተዉ ያለፉ የበርካታ ጀግኖች አላማና እምነት መሬት ወድቆ ከመቅረት ይልቅ በእነሱ ምትክ በሚተኩ ሌሎች እልፍ ተከታዮቻቸዉ ብርቱ ትግልና ጽናት የተሰዉለት አላማ ዳር ሲደርስና ግቡን ሲመታ ከአንደም ሺህ ጊዜ የተመለከትነዉ። በሌላ በኩል ሰዉን /ትዉልድን/ ከተሰፈረለት ርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓካንዳ ዉጭ ሌላ ምንም ነገር እንዳያይ፣ እንዳይሰማና እንዳይጠይቅ አይኑን በመጋረድና ጆሮዉን በመድፈንና እንደ ጋሪ  በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዳይ ማሰገደድ ግን አካላዊ ስጋን ከመገደልም በላይ ባህልን፣ እምነትን፣ ሀገርን፣ መግደል ነዉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ የነበረዉን ሀገራዊ ማንነትን በማጥፋት አላማ የሌለዉ ትዉልድን መፍጠር ነዉ።  

ኢህአድግም ቢሆን ይህንኑ ጠንቅቆ ያዉቃልና ይህንኑ ስልት ላለፉት 20 አመታት በሚገባ ተጠቅሞበታል። ምናልባት በኢሀድግ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ መንግስት ከሚደሰኩረዉ ርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ በተጨማሪ ሌሎች አማራጮችንና አቅጣጫዎችን ለመታዘብ እድሉን አግኝቷል ከተባለ በ1997 ዓ.ም በነበረዉ ሀገራዊ ምርጫ  ወቅት ሲሆን ዜጎች እንድህ አይነት አይቸዉን ሊገልጡላቸዉ የሚችሉ አጋጣሚዎችን የማግኘትና የመታደም እድል ካገኙ ምን ሊከተል እንደሚችል በተግባር አይቶታልና ድሮም በመንግስት ችሮታ ተከፍቶልን የነበረዉ የጭላንጭል በር ለአንደና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያዉም በባሰ መልኩ በራሱ በመንግስት እጅ ተጠርቅሞ ተዘግቷል። ይህ የመንግስት የተንሻፈፈ አካሄድ ያስከተለዉን ዉጤትና ሀገራዊ ኪሳራ ደግሞ እየመረረንም ቢሆን ሳንወድ እየተጋትነዉ እንገኛለን። 

  • ብሔራዊ ስሜቱ የዘቀጠና ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰዉ ሆኖ ከመፈጠር አዉሮፓ ዉስጥ ድንጋይ አሊያም የአበባ ማስቀመጫ ሆኖ መፈጠር ይሻሻላል! የሚል ትዉልድ በኢህአድግ ዘመን እንጅ በሌላ በየትኛዉም ዘምን አልተሰማም
  • ትናንት እነዋለልኝ መኮንን የመሰሉ  አርቆ አሳቢዎች የአገራችንን የብዙ ሺህ ዘመን ታሪክ ይበክላል በማለት በሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ ሊካሄድ የነበረዉን የሴቶች የአጭር ቀሚስ ትርኢት በመቃዎምና ከዝግጅቱ ጀርባ የነበሩት የዉጭ ሀገር ዜጎች ትምህርት ቤቱን በመጠቀም የባዕዳንን (የራሳቸዉን) ባህል ለማስፋፋት አሲረዋል በሚል ከአገር እንዲባረሩ በተሟገቱላት ሉዋዕላዊት ሀገር ግብረ ሰዶማዊ አዳሪዎች ያለ እፍረት አደባባይ ቆመዉ ደንበኞቻቸዉን የሚጠብቁባትና ዋጋ የሚደራደሩባር፣ አልፎ ተርፎም ኢትዮጵያን ወክለዉ የቁንጅና ዉድድር የሚያደርጉባት አገር በኢህአድግ ዘመን እንጅ በሌላ በየትኛዉም ዘምን አልታየችም
  •  ስለ እራሱ የተለያዩ ሀገራዊና ፖለቲካዊና ታሪክ እዉነቶች ከመጠየቅና ከመዎያየት ይልቅ ሌሎች የምዕራባዊያን እንቶፈንቶ ወሬዎች ለመስማትና ለማዎቅ የሚዋትት ትዉልድ አልፎ ተርፎም የራሷ ጉዳይ  ኢትዮጵያ ለኔ ምን አደረገችልኝ? የሚል ከንቱ ትዉልድ በኢህአድግ ዘመን  እንጅ በሌላ በየትኛዉም ዘመን አልታየም
  • ስለ አድዋ ጦርት ወይም ስለ አጼ ቴዎድሮስ የማይበገር ክንድና ለእናት ሀገራቸዉ ስለከፈሉት ዋጋ ከመመስከርና ከመዘከር አልያም በፍትህ እጦት ስለሚሰቃዉ ዜጎች ለምን ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ ስለ ሪሃና አለባበስና አዋዋል መደስኮር የሚቀናዉ የዩንቨርስቲ ተመራቂ በዚሁ በበኢህአድግ ዘመን  እንጅ በሌላ በየትኛዉም ዘመንና ጊዜ አልታየም
አዎ አሁንም ሀገራችንን ኢትዮጵያን ያለቸበት ሁኔታ በአንክሮ ለሚታዘብ ቅን ዜጋ ያለንበት ሁኔታ ከዚህም በላይ የከፋ ነዉ። እኛ እንደዜጋ ማንም የፈለገዉን የመደገፍ፣ የመምረጥና የመከተል መብት እንዳለዉ እናዉቃለን እናከብራለን። ይህ ግን ዜጎችን ምንም አይነት አማራጭ እንዳይኖራቸዉ በማድረግና በተመሳሳይ መረጃ ስለተመሳሳይ ነገር ብቻ እስኪያቅለሸልሻቸዉ ድረስ በመደስኮርና በማደንዘዝ መሆን ግን የለበትም። ከዚህ ይልቅ ዜጎች ስለሚፈልጉት ነገር የሚፈልጉትን መረጃ የማግኝት፣ የማንበብ፣የመተንነተን፣ የመተቸትና የማስተላለፍ መብት ተጠብቆ መሆን አለበት የሚል ጽኑ እምነት አለን። ይህም በአድዋ ጦርነት ወቅት አጼ ምኒልክ ማሸነፋቸዉን ደበቅነዉም አልደበቅነዉም እዉነታዉ አይለዎጥምና ነዉ። በ 3 ሺህ ዘመን ታሪካችን በተለያየ ጊዜና መልክ የመጡብንን ጠላቶቻችንንና አንድነታችንን መሰረት አድርገን አሳፍረን መልሰናቸዋል። ሌላዉ ቀርቶ  ወልዳን ኮትኩታ ባሳደገቻቸዉ የገዛ ዎንሞቻችን የሚደርስብንን ጭቆናና በደል አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ ሳንል አንድ ሆነን ከላያችን ላይ አሽቀንጠረን ጥለናቸዋል። ይህም ተስማማንበትም አልተስማማንበትም አገድነዉም ፈቀድነዉም ከእዉነታነቱ የሚለዉጠዉ አንዳች ነገር የለም። አዎ አሁንም በድጋሜ እዉነትን በማፈን አልያም ወደ ዉሸት በመቀየር መደበቅ/ማጥፋት/ እንደማይቻል በአጽኖት ለመግለጽ እንዎዳለን።
 
በተጨማሪም ከናተ ጋር ባሳለፍናቸዉ ጥቂት ቀናት ዉስጥ አጋጣሚዉንና እድሉን የማግኘትና ያለማግኘት ጉዳይ እንጅ ማንም ኢትዮጵያዊ ስለ ሀገሩ ለማዎቅ፣ ለመወያየትና አብሮ ለመስራት ብርቱ ፍላጎት እነዳለዉ መታዘብ ችለናል። ስለሆነም ለነበራችሁ ቆይታ፣ ላደረጋችሁልን ትብብርናና ቀና አስተያየት ከልብ እያመሰገንን ጦማራችን ያላችሁበት ድረስ ለመድረስ የምታደርገዉን ትግል እንደምትቀጥል እየገለጽን መፍትሔ እስከምንፈልግ ድረስ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያላቸሁ ወዳጆቻችን በፌስ ቡክ ፔጃችን በኩል እንድትከታተሉን በትህትና እንገልጻልን።
_______________________________________________
አንድ አገር አንድ ሕዝብ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
(ግንቦት፣ 2004)

------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

No comments:

Post a Comment