Thursday, July 19, 2012

ያለንም እኛ የሞትንም እኛ!

የጠቅላይ ሚንስተር መለስ ዜናዊ በጠና መታምንና ከሚዲያና ከህዝብ አይን መሰዎር ሰሞኑን በህዝቡ ዉስጥ ለሚናፈሱ በርካታ ዉጅብሮች መፈጠር ምክንያት ሆኗል። ተራዉ ህዝብ ይቅርና አስተማማኝ የመረጃ ምንጮች አሉን የሚሉ ጋዜጠኞችን እንኳን ሳይቀር ለዉዥምብር የዳረገ ክስተት ነበር የሰሞኑ የጠቅላይ ሚንስተር መለስ የመታመም ዜና። የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ ጠቅላይ ሚንስተር መለስ ዜናዊ ህክምናቸዉን አጠናቀዉ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸዉን ከታማኝ ምንጮች አረጋግጫለሁ ሲል፤ የጠቅላይ ሚንስትሩን መታመም አስመልክቶ አንዳችም ነገር ትንፍሽ ሳይል የሰንበተዉ  የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አማረ አረጋዊ በበኩሉ ጠቅላይ ሚንስተር መለስ ህክምናቸዉን አጠናቀዉ ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸዉንና በተሻለ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ፣ ነገር ግን በቅርብ ቀን ስራ እንደማይጀምሩ ዘግቧል። በሌላ በኩል የፈረንሳይ የዜና አገልግሎት የሆነዉ ኤ.ኤፍ.ፒ ጠቅላይ ሚንስተር መለስ ዜናዊ በጠና እንደታመሙና አሁንም ድረስ ቤልጀም ብራሰልስ በሚገኝ ሆስፒታል ዉስጥ በህክምና ላይ እንዳሉ በዜና ዘገባዉ አሰራጭቷል። 

 

Thursday, July 5, 2012

በኢትዮጵያ የመጀመሪያዉ/ን…

 መቸም ኢትዮጵያ ዉስጥ አድስ የተጀመረን ነገር ወይም የነበረን አገልግሎት ሲቻል  በአለም፣ ካልሆነ በአፍሪካ እነዚህ ሁለቱ ካልተሳኩ ደግሞ “በኢትዮጵያ የመጀመሪያዉ” በሚል ተቀጥላ ማስተዋወቅ በህግ ተደንግጎ የተቀጠ ግደታ እስከሚመስል ድረስ  ከግለሰብ እስከ መንግስት ተቋማት ድረስ የተለመደ ነዉ። ምናልባትም የዚህ አይነት የማስታዎቂያ ተቀጥላዎችን በብዛት በመጠቀም በአለም የመጀመሪያዎቹ ሳንሆን አንቀርም (lol አላችሁ!)።  በእዉቀቱ ስዩም “የቤተሰቦቼ ሁለተኛ ልጅ በመሆን የመጀመሪያ ነኝ”  ሲል በአሽሙር ልክልካቸዉን እንደነገራቸዉ ማለቴ ነዉ፡፡ በርግጥ ከኢትዮጵያም አልፈዉ በአለም ደረጃ ለመተግበር ቀርቶ ለማሰብ እንኳን የሚከብዱ በርካታ ስራዎችን ቀዳሚ በመሆን ያበረከቱ አሊያም ያስተዋወቁ የትየለሌ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ እሙን ነዉ። እነዚህን ኢትዮጵያዊያንም “የመጀመሪያዉ” በሚል የማሞካሻ የማዕረግ ተቀጽላ መጠራት ቢያንሳቸዉ እንጂ የሚበዛባቸዉ አይሆንም። ምናልባትም ዛሬ ላይ ያሉ ማስታዎቂያ ነጋሪዎችም በእዉቀቱ እንዳለዉ “የመጀመሪያዉ” የሚለዉን ተቀጽላ “እግዚያብሔርም በመጀመሪያ ሰማይና ምድርን ፈጠረ” ከሚለዉ የመጸሐፍ ቅዱስ ቃል ሳይሆን ከነዚህ ኢትዮጵያዉያን የክብር ስም ላይ ይሆናል ላፍ አድርገዉ የወሰዱት።