Friday, May 18, 2012

ጦር ያዘሉ ግጥሞች

አክሱምን አቃጥሉት!
==================
በስዉር-በስዉር ሳታወጡ ይፋ
አክሱምን አቃጥሉት ላሊበላም ይጥፋ!
ሁሉም ቢተባበር የሚያቅት አ’ደለም
ጢያና ጀጎልን ባንድ ላይ ለማዉደም
መስጅድ፣ ቅርሳ ቅርሱ፣ ፍልፍል ቤተ-መቅደስ
በዘዴ-በዘዴ በየተራ ይፍረስ 
የጥበብ መጸሐፍት ጥንታዊ ብራና
በእሳት ይቀጣጠል ጋዝ ይርከፍከፍና!!
የአያቶቹ ጥበብ ደብዛዉ የጠፋበት
ለምን ይኸ ትዉልድ ወቀሳ ይብዛበት?
አክሱም፣ ፋሲል ግምብን ማቃጠል ነዉ ጥሩ
በዘመናችን ላይ እንዳይመሰክሩ!!
ሳማይቱ ኑሮ
=============
ይኸ ነወይ ኑሮ? ይኸ ነወይ እድሜ?
ጆሮና አይኔን ይዠ አልመጣም ደግሜ
አልቃሻ ልቤማ ጭራሽ ጉጉ አ’ደለም
በጠማማ ማገር ለተሰራች አለም
ፍትህና እዉነትን አለቅጥ ብጠማ
ቅፅል ስሜ ሆኗል መንፈሰ-ደካማ
አልመጣም! አልመጣም! አልመጣም ደግሜ!
እናተዉ ኑሩበት በአሸሸ ገዳሜ
በነፍስ፣በልቤ፣ በደሜ ዉስጥ ያለዉ
የእኔ ህይወትና የእኔ አለም ሌላ ነዉ።
_________________
ሰለሞን ሞገስ (ፋሲል)
እዉነት ስቀሏት!-2001 ዓ.ም

ሰሞነኛ 
==========
 በሌለ ቅዳሴ ሰሞነኛ በዝቶ ስንዴ እንደወረዛ
እነደ ዘኬ ቆሎ ዝና እየተነዛ
ትናንት ለጉድ ተብሎ ለዛሬ ጠነዛ
ማታ ተድመንምኖ ጧት ሆነብን ጤዛ
ፅዋ እንደሚረከብ የአቦ ባለተራ
እንዳፈረሰ ቄስ የፅጌ ደብተራ
ስም ሰሞነኛ ነዉ ገኖ ‘ሚሆን ተራ።
ልናነጋ ተኛን
===============
ጨለማ ሲገዝፍ በቀን እኩይ ድርጊት
ዝንተ ዓለም ሳይናድ የጨለማ ምርጊት
በድሜጥሮስ ኩፋል “ ቀን-ጨለማ” እያልን
ልንዉል ተነስተን ልናነጋ ተኛን
በድሜጥሮስ ኩፋል
በገማ ጭንቅላት ጨለማ እየቆጠርን
እንደ ወፏ ሞረሽ በማያነጋ ድምፅ ሁሌ እየተብላላን
አንድ ቀን ሳንዉል ሦስት ሺ ዓመት ሞላን
______________________________
ይስማዕክ ወርቁ
የወንድ ምጥ-1999 ዓ.ም

መልክአ ህይወት
=============
አዳኝ በንስሐዉ፣ ሰይፉ አልዶለዶመም
ታዳኝ በጾለቱ፣ ካራጆች አልዳነም
ተኳሹ ቢዋልል አልመታ ቢል ተኩሱ
ካፈሙዝ ይጠጋል ኢላማዉ እራሱ።

ነጠብጣብ ሀሳቦች
=============
ሰማይ ከሚከን ይፀንስ መከራ
ያርግፍ! ያርግፍ! ያርግፍ! መአት እያፈራ
የ’ሣት ዛፍ ባለበት ሰደድ ላያስፈራ።
***
ከሐምሌት ጋር ሞቷል፣ የማመንታት አለም
ከሆኑ በሗላ ፣ አለመሆን የለም
ሸክም ፀጋ ሆኗል ፀጋህን አትግፋ
በጠባብ አልም ዉስጥ ትክሻህን አስፋ
***
አንድ ህልም እንደ ጠጅ፣ እየደጋገሙ
ንግር፣ ትንቢት ሳይሆን ታሪክ እያለሙ
ተኝቶ መነሳት አቤት ሲያቅለሸልሽ
ጌታ ሆይ አትንሳት ነፍሴን እንቆቅልሽ።
__________________
በእዉቀቱ ስዩም
የ’ሣት ዳር ሐሳቦች-2000 ዓ.ም

እንዳይነግርህ አንዳች እዉነት!
=====================
ደንስ ጎበዝ! ደንስ ጀግና
ክራቫትክን አዉልቅና
ሃሳብክን ልቀቀዉና
ኮትክን ሸሚዝህን ጣልና
ርገጥ፣ጨፍር፣ደንስ ጀግና!
                ያን የሙዚቃህን ናዳ፣ የኮንትራባሱን መብረቅ
                ልቀቀዉና ይድብለቅለቅ
ምድር በሆይታ ይጥለቅለቅ!
ምንም እንዳታስብ፣ ሁሉን-ሁሉን እንድትረሳ
ደንስ! ካካታዉ ይነሳ
ጨፈር፣ ወለሉ እስኪበሳ…
ሃይ-ሃይ፣ዋይ!ሃይ-ሃይ!በልበት
የጃዝ ፋንፋር አንኳኳበት
ራስክን እንዳታስብበት
ሆ!በል እሪ!በል ምታበት
ፎክርበት፣ አቅራራበት
አናፋበት፣ ሸልልበት
የሲቃ ሳቅ አስካካበት
ሆያ-ሆዬ! በል ጩህበት
ኡኡታህ ምንኮራኩርክን፣ እስኪያሰጥመዉ አጓራበት
ጭንቅላትክን ግዘፍበት፣ ዉቀጥበት፣ ዉገርበት…
ዝግ ብሎማ ያሰበ እንደሁ፣ ይነግርሀል አንዳች እዉነት።
_________________
ሎሬት ፀጋየ ገ/መድህን
እሳት ወይ አበባ-1966

አንተ ጎጆ ቀላሽ
==========
አንተ ጎጆ ቀላሽ
አንተ ቤተ ሰሪ
ድንጋዩን ፈንቅለዉ
ጉቶዉን መንግለዉ
ጥረገዉ ደልድለዉ
ርሰሰዉ ቸልሰዉ
ይጥበቅ መሰረቱ
ከስር እስካናቱ።
እንዲያማ ካልሆነ፣
ድንጋይ በድንጋይ ላይ በተነባበረ
አሸዋ ጠጠሩ፣ ስሚንቶ ብረቱ፣ እየቅል ካደረ
ላምል ለግብር ይዉጣ፣
ሁሉም በየፊናዉ በተዉሸልሽሎ
ስልት፣ ከተዉተረተረ
ጎጆም አልተሰራ፣ ኑሮም አልተኖረ።
__________________
አለማየሁ ገ/ሕይወት
እታለም-1978
ጥሬ ጨዉ
=========
መስለዉኝ ነበረ
የበቁ የነቁ
ያወቁ የረቀቁ
የሰዉ ፍጡሮች
ለካ እነሱ ናቸዉ
ጥሬ ጨዉ…ጥሬ ጨዉ ጥሬ ጨዋዎች
መፈጨት-መሰለቅ-መደለዝ-መወቀጥ-
መታሸት መቀየጥ
ገና እሚቀራቸዉ
“እኔ የለሁበትም!”
 ዘወትር ቋንቋቸዉ።
___________
ደበበ ሰይፉ




------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

No comments:

Post a Comment