Wednesday, June 27, 2012

የአፄ ሀይለ ሥላሴ እናት ማን ናቸዉ?


ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ የሚለዉ መጽሐፍ ላይም ይሁን በማንኛዉም አጋጣሚ ልጃቸዉ ቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ የእናታቸዉን ፎቶግራፍ አሳይተዉም ሆነ የአባት ስም ተናግረዉ አያዉቁም። ታሪክ ጸሐፊዎችም በመፍራት ሊሆን ይችላል የቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴን የአባት ወላጆች ሲዘረዝሩ የእናታቸዉን አባት ስም ግን አይጠቅሱም። የሚገርመዉ ደግሞ  ከልጃቸዉ ህልፈተ ሕይወትም በሗላ የእናታቸዉን አባት ስም በጽሑፍ ወይም በይፋ ለመጥቀስ ብዙዎች እስካሁን አልደፈሩም። ስለኾነም በምንም ይፋ ነገር ላይ የወይዘሮ የሺ እመቤት (የአፄ ሀይለ ሥላሴ እናት) ምስል ለሕዝብ አልተናኘም። ወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ ወይም ወይዘሮ ቂቶ የወይዘሮ የሺ እመቤት እናት ቁመታቸዉ አጭር ሲሆን ብስል ቀይና በጣም ዉብ የሆኑ ሴት ነበሩ። ትዉልዳቸዉም የስልጤ ጉራጌ ናቸዉ ይባላል። ከአንዲት ጉራጌ የሚወለድ ልጅ ትልቅ ንጉስ ይሆናል የሚል ትንቢት ስለነበረ የሸዋ መኳንንት ሁሉ የጉራጌ ሚስት እየፈለገ ያገባ ነበር። በተለይ የወለኔ ሴቶች ቆንጆዎች ስለነበሩ ብዙ መኳንንቶች ተረባርበዉባቸዋል። ወለኔ ወሊሶ ከተማ አጠገብ ያለ አገር ሲሆን ነዋሪዎቹ ጉራጌዎች መልካቸዉ ቀያይና ቆንጆዎች ስለሆኑ ይመረጡ ነበር። የመኳንንቶቹ አማራ ሚስቶች በቅናት ጉራጌዎቹን ሴቶች “ምርኮኞች” ይሏቸዉ ነበር። ራስ ዳርጌ ወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስን በይፋ ሚስትነት ሳይሆን በዕቁባትነት አስቀምጠዉ ሦስት ልጆች ወልደዋል። ይሁንና ወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ ሌሎች ልጆችም ከተለያዩ ሰዎች ወልደዋል።

Wednesday, June 20, 2012

ግን ለምን እንፈራለን? (ክፍል አንድ)


የአለፈዉ ሳምንት አድስ ጉዳይ መጽሔት አብይ አርዕስት አድርጎ ይዞት የወጣዉ ሀሳብ በአሁኑ ወቅት ያሉትን የኢትዮጵያ ምሁራንን በፍርሃት ተሸብቦ የመቀመጥን ነገር ነበር።  አድስ ጉዳይ “የፍርሃት ሀገር ዜጎች፣ ‘ኦሜርታ’!” በሚል አርዕስት ይህንኑ ጉዳይ የዳሰሰበትን ማራኪ ጽሁፍ ያስነበበን ሲሆን እነዚህኑ ከልክ ባለፈ ፍርሃት ተሸብበዉ የሚገኙ የዘመናችንን ምሁራንን፣ “ዉሃ ዉስጥ ተኝተዉ የሚያልባቸዉ ምሁራን” ሲል ነበር የገለጻላቸዉ። በርግጥም አዋቂና ችግር ፈች የሚባለዉ የአንድ ሀገር የተማረ ዜጋ የራሱንና የሌሎችን መብት ለማስከበር ከመትጋት ይልቅ በፍርሃት ተሸብቦና ተሳስስሮ ከተቀመጠ ቢያንስ መብትና ግደታዉን እንኳን በቅጡ ለይቶ የማያዉቀዉ ሌላኛዉ ያልተማረ ህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ከፍርሃትም በላይ በሆነ ጭንቅ ዉስጥ እየኖረ እንደሆ መገመት አያዳግትም።

Friday, June 1, 2012

የመዝሙረ ዳዊት ሚስጥሮች


መጸሐፍ ቅዱስ  በአለማችን በብዛት ከተነበቡና ወደ በርካታ የተለያዩ የአለም ቋንቋዎች ከተተረጎሙ መጸሐፍት መካካከል አንዱና ምናልባትም በአንደኝነት ሊጠቀስ የሚችል መጸሐፍ መሆኑ አያጠራጥርም። ምንም እንኳን መጸሐፍ ቅዱስን ማን ጻፈዉ? የሚለዉ ጥያቄ በተለያዩ ሰዎች የተለያየ መልስ የሚሰጥበት አከራካሪ ጉዳይ ቢሆንም  እንደዛሬዉ መጸሐፍት እንደልብ ባልነበሩበት ዘመን ለብዙዎች የጥበብ ምንጭና የእምነት መንገድ ጠራጊ የሆነ፣ ዛሬም ድረስ ክርስትናን የእምነት ፍልስፍናቸዉ መሰረት ላደረጉ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች የእምነት-ማዕዘን በመሆነ እያገለገለ ያለ ታላቅ መጸሐፍ ነዉ፣ መጸሐፍ ቅዱስ። መጸሐፍ ቅዱስ በዋናነት ብሉይ-ኪዳንና አድስ-ኪዳን በሚባሉ ሁለት መሰረታዊ ክፍሎች (ቅጾች) የተዋቀረ መጸሐፍ ሲሆን እነዚህም ሁለት ቅጾች እያንዳንዳቸዉ በርካታ ምራፎችንና የመጸሐፍ ክፍሎችን በዉስጣቸዉ አካተዉ የያዙ ናቸዉ።  ከነዚህ በርካታ የመጸሐፍ ክፍሎች መካከል “መዝሙረ ዳዊት”  በመጀመሪያዉ የመጸሐፍ ቅዱስ ቅጽ (በብሉይ ኪዳን) ስር ተካቶ የሚገኝ የመጸሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲሆን ምንም እንኳን “መዝሙረ ዳዊት” መቸና በማን ተጻፈ የሚለዉ ጉዳይ  አከራካሪና እራሱን የቻለ ጥናትን የሚፈልግ ጉዳይ ቢሆንም