Tuesday, May 22, 2012

እዉን የአይጥ መያዣ ወጥመድ ላምን አያሰጋትም?

በአንድ መለስተኛ የገበሬ ጎጆ ቤት ዉስጥ የሚኖሩ ሶሰት የተለያዩ የቤት እንስሳቶች (አንድ ዶሮ፣ አንድ አሳማና አንድ ላም) ስብሰባ ላይ ተቀምጠዋል ። ዋናዉ የተሰበሰቡበት ምክንያት ደግሞ ቁጥራቸዉ ትንሽ በመሆኑና ሁሉም አንድ አንድ ብቻ በመሆናቸዉ የሆነ ችግር ወይም አደጋ ቢገጥማቸዉ በተናጥል ለመከላከል ከባድ መሆኑን በማመናቸዉና ይህንኑ አሳሳቢ ችግር እንዴት በጋራ ህብረት ፈጥረዉ መከላከል እንዳለባቸዉ ዉይይት ለማካሄድና የጋራ ስምምነት ላይ ለመድረስ  ነዉ። ሶስቱም ለብዙ ሰአታት ከተከራከሩና ከተጨቃጨቁ በሗላ፣ “ሁሉም  ቤት ዉስጥ የሚደረግን ማንኛዉም እንቅስቃሴ በንቃት መከታተል እንዳለባቸዉና ለሶስታቸዉም አልያም ከሶስታቸዉ ላንዳቸዉ ሊያሰጋ የሚችልን ማንኛዉንም እንቅስቃሴ ሲደረግ ያየ አልያም የሰማ አካል ለሌሎች የቡድኑ አባላት በፍጥነት ማሳወቅ እንዳለበትና ችግሩ በተከሰተ በአጭር ጊዜ ዉስጥም ሶስቱም አስፈላጊዉን ትብብር በጋራ  በማድረግ  ችግሩን መፍታት እንዳለባቸዉ የሚደነግግ የጋራ ስምምነት ላይ ይደረሳሉ።

ሁሉም በዚህ ሀሳብ ተስማምተዉ ሊለያዩ ሲሉ ድንገት አይጥ በአጠገባቸዉ ስታልፍ ስላየቻቸዉ ስብሰባዉን ባለቀ ሰአት ተቀላቀለችና ለምን እንደተሰበሰቡ ትጠይቃለች። እነሱም የስብሰባዉ አጀንዳ የነበረዉን ዋና ጉዳይና መጨረሻ ላይ የደረሱበትን ውሳኔ በዝርዝር ያስረዷታል። አይጥም ነገሩን በጥሞና ካዳመጠች በሗላ እሷንም የቡድኑ አባል ቢያደርጓትና የዚህ የትብብር ማዕቀፍ አንድ አካል ብትሆን ምን ያህል ደስተኛ ልትሆን እንደምትችል በመግለጽ ልታበረክት የምትችለዉን አስተዋጾ ሳይቀር በዝርዝር እየጠቀሰች የእባካችሁ አባል ልሁን ጥያቄዋን ታቀርባለች። በመጨረሻም ሶስቱም በጉዳዪ ላይ ለአጭር ጊዜ ከተወያዩበት በሗል አይጥ አባል እንድትሆን ተስማሙና ስብሰባዉ ተበተነ።

ይህ ስምምነት በተደረገ አራተኛዉ ቀን ላይ ነዉ። አይጥ በግርግዳ ቀዳዳ አሾልካ ባልና ሚስት የሆነ የተጠቀለለ ነገር ሲፈቱ በአፅንኦት እየተመለከተች ነዉ።  ምን አይነት ምግብ ቢሆነዉ እንደዚህ በአማረ መጠቅለያ የተጠቀለለዉ? አለች አይጥ በአድናቆት አሁንም በግርግዳዉ ቀዳዳ አይኖቿን አጮልቃ በትኩረት እየተመለከተች። ጥቅሉ ተፈትቶ ሲያልቅ ግን  ያየችዉን ነገር ፈጽሞ ማመን አቃታት። እንደዛ በአማረ መጠቅለያ ተሸፍኖ የነበረዉ የሚያስጎመጅ የምግብ አይነት ወይም ሌላ ነገር ሳይሆን ዘመናዊ የአይጥ መያዣ ወጥመድ ነበር። እናም ነገሩን በድንጋጤ ክዉ ብላ ከተመለከተች በሗላ ከሌሎች እንስሳቶች ጋር ቀደም ሲል በገባቸዉ ዉል መሰረት አድስ ተገዝቶ ስለገባዉ የአይጥ ወጠመድና ሊያደርግ ስለሚገባዉ ጥንቃቄና የጋራ የመፍትሄ ርምጃ ለመነጋገር አባላቶቹን ፍለጋ ጊዜ ሳታባክን መሯሯጥ ትጀምራለች።

መጀመሪያ ያገኘቻት ዶሮ ነበር። አይጥም ዶሮን እንዳየቻት ቁና ቁና እየተነፈሰች፣ “ዶሮ ሆይ! እነሁ እዚህ እኛ የምንኖረበት ቤት ዉስጥ አድስ የአይጥ መያዣ ወጥመድ ተገዝቶ እንደገባ በአይኔ በብረቱ አይቻለሁና በስምምነታችን መሰረት ጥንቃቄ እንድታደርጉ ላሳዉቃችሁና በዉላችን መሰረትም በአስቸኳይ ለችግሩ መፍተሄ በጋራ እንድናፈላልግ ላስመዘግባችሁ ስበር ወደ እናተ እየመጣሁ ሳለ ነዉ የተገናኘ ነዉ” ስትል አስረዳች። ዶሮም ሁሉንም በጥሞና ካደመጠች በሗላ ይገርማል በሚል አስተያየት አይጥን እየተመለከተች፣ “ወዳጄ አይጥ ሆይ፣ በእዉነቱ ይህ ነገር ከማንም በላይ አንችን የሚመለከት አደጋ እንደሆነ ሳልነግርሽ ማለፍ አልፈልግም። ነገር ግን ይኸ ችግር እኔን ፈጽሞ አይመለከተኝምና ልጨነቅበት ቀርቶ ከነጭራሹ ትርጉምም የማይሰጠኝ ጉዳይ በመሆኑ ለእኔ ለመንገር የዚህን ያህል መድከም አልበረብሽም።” በማለት እቅጩን ትነግራትና ቻዉ እንኳን ሳትላት በቆመችበት ትታት ትሄዳልች።

አይጥ ምንም እንኳን በዶሮ አኳኳሗን ብታዝንም ተስፋ ሳትቆርጥ ሌሎቹን የቡድኑ አባላት ፍለጋዋን ትቀጥላለች። ትንሽ ወዲያ ወድህ ካለች በሗላም አሳማን በረት ዉስጥ ተኝቶ ታገኘዉና በተመሳሳይ መንገድ ስለመጣችበት ጉዳይ ታስረዳዋለች። አሳማም ስለሆነዉ ነገር ሁሉ በጽሞና ካዳመጠ በሗላ። “ወዳጄ አይጥ ሆይ! በእዉነቱ ለአደረግሽልኝ  ነገር ሁሉ ሳላመሰግንሽ ማለፍ አልፈልግም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ችግሩ አንቺኑ ብቻ  የሚመለከት ነዉና ይኸን መስማት እጅግ በጣም ያሳዝናል። ነገር ግን ከመጸለይና ከዚህ ነገር እንዲያተርፍሽ አምላኬን ከመለመን ሌላ ምን ላደርግልሽ እችላለሁ? እንዴትስ ልረዳሽ እችላለሁ? በአንድ ነገር ብቻ ግን እርግጠኛ ሁኝ በጾለት አረሳሽም ።” በማለት ያጽናናትና ያሰናበታታል።

አይጥ የቀረችዉን የመጨረሻ የቡድኑ አባል የሆነችዉን ላምን ለማግኘትና ቁርጧን ለማዎቅ መስክ ላይ ሳር በመጋጥ ላይ ወዳለችዉ ላም በመሄድ ቀደም ሲል አግታቸዉ ለነበሩት የቡድኑ አባላት በገለጸችበት አኳሗን ጉዳዪዉን ለላም በዝርዝር ታስረዳታለች። ላምም እንደሌሎቹ እንስሳቶች ሁሉ አይጥን በመገረም ካስተዋለቻት በሗላ፣ “ወዳጄ አይጥ ሆይ!በእዉነቱ ይችግር አንቺ ላይ በቀጥታ ያነጣጠረ ችግር ነዉና ስለተፈጠረዉ ነገር ሁሉ በጣም አዝናለሁ ነገር ግን ይኸ ጉዳይ አንዳችም ከእኔ ጋር የሚያገናኘዉ ነገር አይኖርምና እኔን ለመንገርና ለማስጠንቀቅ ይህን ያህል መድከም አልነበረብሽም። እኔ ደግሞ ታዉቂኛለሽ በሰዉ ጉዳይ ገብቶ መዳከር አልወድም እናም ይቅርታ አድርጊሊኝና ምንም ልረዳሽ አልችልም” በማለት ታሰናብታታለች። አይጥ ከዚህ ሁሉ ጥረትና ዉጣ ዉረድ በሗላ ወዴትም መሄድን አልፈለገችም። ችግሩ እሷ እራሷን ብቻ የሚመለከት መሆኑን ሁሉም እየደጋገሙ  ነግረዋታልና በሀዝንና በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተዉጣ የመጣዉን ነገር ሁሉ ራሷ በብቸኝነት ለመጋፈጥ ቆርጣ ወደ ቤቷ ገብታ ትተኛለች።

የዛኑ ቀን ሌሊት አድሱ የአይጥ መያዣ ወጥመድ የሆነ ነገር እንደያዘ በሚያሳብቅ ድምጽ ድንገት ያምባርቃል። ወድያዉኑ የገበሬዉ ሚስት ከእንቅልፏ ተነስታ እየተጣደፈች ወጥመዱን በጨለማ መሀል በዳሰሳ መፈለግ ትጄመራለች። ብዙም ሳትቆይ ግን  እሷ እራሷ ቤቱን እንደገና በጩኸት ትሞላዋለች። ወጥመዱ ይዞ የነበረዉ ምስኪኗን አይጥ ሳይሆን  የአንድ አደገኛ ተናዳፊ እባብን ጅራት ነበርና በጨለማዉ ዉስጥ በእጇ እየዳበሰች ሳለ ጅራቱን ተይዞ ሲወራጭ የነበረዉ እባብ  ስለ ነደፋት ነበር መጮዃ።  ጮኸቷ ያባነነዉ ባሏም ወድያዉኑ ወደ ሀኪም ቤት በመዉሰድ አስፈላጊዉን ህክምና እንድታገኝ  በማድረጉ ከህመሟ አገግማ ወደ ቤቷ ትመለሳች። ነገር ግን እየዋለ እያደረ ሲሄድ ከህመሟ ፈጽማ ልትድን አልቻለችም። እንደዉም ከቀን ወደ ቀን ህመሙ እየባሰባት ይሄዳል። በዚህ ጊዜም ልጠይቋት ከሚመላለሱት ሰዎች ብዙዎቹ የዶሮ ሾርባ በተከታታይ ብትጠጣ ልትጠነክርና ልትድን እንደሚትችል ደጋግመዉ ሀሳብ በማቅረባቸዉ ባሏ ቤት ዉስጥ ያለችዉን ብቸኛ ዶሮዋቸዉን በማረድ በየቀኑ  የዶሮ ሾርባ ሚስቱን እያጠጣ ማስታመሙን ይቀጥላል። ነገር ግን አሁንም ሴትዮዋ ከህመሟ ልታገግም አልቻለችም። ብዙ ሰዎች ግን የአሳማ ስጋ ብታገኝና እሱን ብትበላ በርግጠኝነት እንደምትድን ሀሳብ ያቀርባሉ።  ባልም ይህንኑ በደስታ ተቀብሎ ቤቱ ያለዉን ብቸኛ አሳማ በማረድ ሚስቱን እያበላ አሁንም ማስታመሙን በተስፋ ይቀጥላል። ነገር ግን አንዱም መላ ሳይረዳ ይቀረና ሚስቱ ትንሽ ቀን እንደቆየች ትሞታለች። በዚህም ጊዜ ከቅርብም ከሩቅም ያሉ በረካታ ዘመዶቻቸዉ መሞቷን ሲሰሙ ለቀብር እየተግተለተሉ  በመምጣታቸዉና ያን ሁሉ ለቅሶ ደራሽና አዘንተኛ የሚያስተናግድበት ሌላ ምንም አይነት አመራጭ ስላልነበረዉ ባል አሁንም ቤቱ ዉስጥ የቀረችዉን አንድያ ላሙን በማረድ አዘንተኛዉን በክብር አስተናግዶ ይሸኛል። ይኸ ሁሉ ሲሆን ግን አይጥ አሁንም በዛዉ በተሰነጠቀ የግርግዳ ቀዳዳ በኩል አጮልቃ ትመለከት ነበር።
***
ይህ የእንስሳት ታሪክ ለልጆች ማስተማሪያ አንድሆን የተዘጋጀ አጉል ተረት ቢመስልም ልብ ብሎ ለሚያስተዉለዉና ለሚመረምረዉ ማንኛዉም ሰዉ ግን ከተራ ተረትነትም በላይ በዉስጡ ብዙ ቁም ነገሮችን አጭቆ የያዘ ተረት መሳይ ታላቅ እዉነት መሆኑን ለመገንዘብ አይቸገርም። እኔም ይህን ታሪክ ለጽሁፌ መንደርደሪያነት እንዲሆን የፈለኩት እንድሁ በተረት ዘና ላደርጋችሁ አስቤ ሳይሆን እኛ ኢትዮጵያዊያን አሁን ስላለንበት ነባራዊ ሁኔታ ከታሪኩ ጋር እያነጻጸርኩ አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳትና ጥቂት ነገሮችን ለማለት ስለፈለኩ ነዉ። አገራችን ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤትና የበርካታ ባህሎችና እሴቶች ማህጸን ናት። ጥቁር ህዝቦቿም የዳበረ የመረዳዳትና የመተባበር ባህል የነበረንና ከራሳችን አልፈን ለሌችም  ምሳሌና አርዕያ በመሆን “የጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት” ተብለን እስከ መጠራት የደረስን ኩሩ ህዝቦች ነን። ይህንም የጥቁር ህዝቦች ተምሳሌትነት ማዕረግ ያገኘነዉ እንደ ዛሬዉ እጅና እጋራችንን አጣጥፈን እየደሰኮርን ሳይሆን በተለያየ ጊዜና ወቅት ሳይታክቱ የተነሱብንን የዉስጥና የዉጭ ጠላቶቻችንን፣ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ አልያም ልዮ የጦር ሀይል ሳይኖረን፣ ያለንን የጋራ አንድትና የሀገር ፍቅር ስሜት ብቻ አንግበን በባዶ እግራችን ጦርና ጎራደ አንጠልጠለን እየዘምተን፣ ዘመናዊ የጦር አይሮፕላኖችና የጦር ታንኮችን ከታጠቁ ብረቱ ተዋጊዎች ጋር  በጀግንነትና በአይበገሬነት እየገጠምን በተደጋጋሚ ድል በማድረጋችንና ለነጻነታችንና ለክብራችን ያለስስት ስንዋደቅ የኖርን ህዝቦች በመሆናችን ነዉ።


ከምንምና ከማንም በላይ ይህንኑ ህብረታችንን መሰረት አድረገን በርካታ የማይደፈሩ የሚመስሉ ጠላቶቻችንን ዳግም እንዳይነሱ አድረገን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ታሪካችንና አገራዊ ህልዉናችንን በሞታችን ያጸናን ጥቁር ህዝቦች መሆናችን ማንም ለያስተባብለዉ የማይችል ያገጠጠና ያፈጠጠ እዉነት እንጅ ከልጅ ልጅ ሲተላለፍ የመጣ ተራ ተረት ተረት ባለመሆኑ ነዉ የጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት ተደርገን መወሰዳችን። የዚህ ሁሉ ድልና ስኬት ምስጥር ምንድነዉ? ብሎ ማንም ቅን ሰዉ ቢጠየቅ አልያም ታሪክን ላንዳፍታ ቢመረምር ደግሞ መልሱ “እነዛ የትናቶቹ  ኢትዮጵያዊያን እንደ እሳት በሚነድ የሀገር ፍቅር ስሜት የተለከፉ፣ አትንኩኝ ባይና ከሁሉም በላይ ደግሞ ሀገራቸዉን በሚመለከት ማንኛዉም  ነገር ላይ በጋራ የሚነሱና የሚዘምቱ፣ ተገደዉ ሳይሆን እኔ ልቅደም እኔ ልቅደም እያሉ ሞትን እንደሜዳሊያ ባንገታቸዉ ለማጥለቅ የሚሽቀዳደሙ፣ በሀገራቸዉና በነጻነታቸዉ ጉዳይ ዋዛ የማያዉቁ ብርቱ ጥቁር ህዝቦች ስለነበሩ ነዉ።” የሚል ሆኖ ያገኘዋል።

ይህ ሁሉ ታሪክና እዉነታ ግን ዛሬ ላይ ላለዉ ትዉልድ ነበር እያለ ለባዶነቱ መሙያ የሚሆን ተራ የድስኩር አርዕስት ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ያለዉ አይመስልም። ለተጋረጠቡት ችግሮችና ተግዳሮቶች በአንድነት ከመነሳትና ተባብሮ ከመፍታት ይልቅ እኔን እስካልነካኝ ድረስ ምን አገባኝ በሚል የራስ ወዳድነት ሻሽ አይኑ የታወረ፣ ከሳሎኑ በር ትንሽ እንኳን ፈቅ አድርጎ ማየት የማይችል፣ ከመጠን ባለፈ የግለኝነት (የጎጠኝነት) አዙሪት ዉስጥ ወድቆ የሚዳክር ከንቱ ትዉልድ ነዉ፣ ይህ አድሱ ትዉልድ። በጓደኞቹ፣ በስራ ባልደረቦቹ፣ በጎረቤቶቹ፣ በሀገሩ፣ በታሪኩና በባህሉ ላይ ያነጣጠሩ ችግሮችን በያገባኛል ስሜት ከመቆርቀርና በጋራ ለመጋፈጥ ከመወሰንና እና ነግ በኔ ብሎ በሰባዊይነት ከማሰብ ይልቅ “ለአይጥ የተገዛ ወጥመድ ላምን አያስፈራትም” በሚል ከንቱ ቢህል የሌሎችን ስቃይ እና እንግልት ከመጤፍ የማይቆጠር ልበ-ደንዳና ትዉልድ ነዉ፣ ይህ አድሱ ትዉልድ። ሌላዉ ቀርቶ ለራሳቸዉ የተንደላቀቀና የተመቻቸ ኑሮ መኖር እየቻሉ ነገር ግን ለሀገራቸዉና ለህዝባቸዉ ነጻነት ሲሉ ዋጋ ለሚከፍሉ ጥቂት አገር ወዳድ ሰዎች፣  የትግላቸዉ አጋር መሆኑ ቢቀር እንኳን እየከፈሉት ላለዉ መስዕዋትነት ክብር መስጠት ሲገባዉ ይባስ ብሎ “ጉዳዩ! ምን አባቱ አቀዠቀዠዉ? አርፎ አይቀመጥም ነበር” በሚል ደፋር አንደበት ለራሱ መብትና ነጻነት እንኳን ሳይቀር የሚታገሉለትን ጥቂት ሀገር ወዳድ ሙሴዎች ገፍቶ የሚጥልና የበላበትን ወጨት የሚሰብር የሀገር ሸክም የሆነ ትዉልድ ነዉ፣ ይህ አድሱ ትዉልድ።


በርግጥ ለአይጥ ተብሎ የተዘጋጀ ወጥመድ ላምን አያስፈራት ይሆናል ነገር ግን በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ጎረቤቷ ላይ ያነጣጠረዉ ችግር ቢያንስ ቢያንስ በቀጥታ እንኳን ባይሆን በተዘዋዋሪ ለሷም ጭምር የሚተርፍ የችግር ፈትል ይዞ እንደሚመጣ ግን እሙን ነዉ። ለዚህም ነዉ ማንም ይዉደድም ይጥላም ጎረቤቱ ሰላም እስካላገኘ ድረስ እሱ ሰላምን ሊያገኛት አይችልም የሚባለዉ። ማንም ይዉደድም ይጥላም የሌላዉ ሰዉ ነጻነትና መብት እስታልተከበረ ድረስም እንድሁ የእሱም መብትና ነጻነትም ሊከበርለት አልያም ሊረጋገጥለት አይችልም። እርግጥ ነዉ ሁሉንም ሰዉ ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ መጎተት ወይም እዲመጣ ማስገደድ አይቻልም ከዛ ይልቅ ማንም ሰዉ የፈለገዉን የመምረጥና የሚፈልገዉን ሀሳብ የማራማድ የማይሸራረፍ ነጻነት ሊኖረዉ ይገባል። ወይም ደግሞ ሁሉም ሰዉ የአንድ ፓርቲ ደጋፊ አለያም ነቃፊ ሊሆን እንደማይችልም ግልጽ ነዉ። ይህ ሁሉ ግላዊ ነጻነት እንዳለ ሆኖ ግን ማንም ይሁን፣ ምንም ይሁን፣ከማርስም ይምጣ ከቬኑስ፣ የምንም ሀሳብ አራማጅ ወይም የየትኛዉም ፓርቲ ደጋፊ ይሁን፣ በርካታ በጋራ ሊያወግዛቸዉና ሊታገላቸዉ የሚገቡ ጉዳዮችም እንዳሉትም መዘንጋት የለበትም። ፍትህ ያላግባብ ሲጓደልና ዜጎች ባላቸዉ አመለካከት ብቻ እየተለዩ ለእስርና ለእንግልት ሲዳረጉ ከዳር ቆሞ እንደ ሲኒማ መመልከት በየትኛዉም መመዘኛ ልክ ሊሆን አይችልም።


ዛሬ መምህራን የምንበላዉ አጣን ብለዉ ሲጮሁ አስተማሪ አይደለሁምና ችግሩ አይመለከተኝም ብለህ እጅህን አጣጥፈህ ብትቀመጥ ምናልባት እነሱን ወግቶ የገደለዉ ጦር ተንቅሎ አንተ ጋር እስከሚሰካ ድረስ ብጫቂ እድሜን ይጨምርልህ ካልሆነ በስተቀር አንዳች ፋይዳ  አይኖረዉም። ማንም ይዉደድም ይጥላም ዛሬ ጎረቤቱን በግፍ የበላ ጅብ ነገ ሲርበዉ ወደሱ ቤት መምጣቱ እንደማይቀር ልብ ሊል ይገባል። ሀገራችን ኢትዮጵያ ከምንግዜዉም በላይ እዉነትን እዉነት፣ ሀሰትን ሀሰት፣ ትክክል የሆነዉን ትክክል፣ ስህተት የሆነዉን ደግሞ ስህተት ብሎ በድፍረት የሚናገር የተሻለ ትዉልድን ትሻለች። ሀገራችን ኢትዮጵያ ከምንግዜዉ በላይ ከብሄርተኝነት ጠርዝ ልቆ ሰብአዊነትን የሚያሰቀድሙ የሀገርና የህዝብ ተቆርቋሪ ትዉልድን ትሻለች። አዎ ሀገራችን ኢትዮጵያ የራሱ አሮበት የሰዉን ለማማሰል ሳይታክት የሚማስንን ትዉልድ ሳይሆን ከምንም በላይ ሀገሩን የሚያሰቀደምና ለራሱና ለሌሎች ክብርን የሚሰጥ የተሻለ ትዉልድን ከምንግዜዉም በላይ ትሻለች።
ኑ! አብረን በጋራ አንድነትን እንስበክ። ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
-------------------------------------------------------------------------
አንድ ህዝብ አንድ ሀገር!
ግንቦት-2004


------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

No comments:

Post a Comment