Tuesday, May 22, 2012

እዉን የአይጥ መያዣ ወጥመድ ላምን አያሰጋትም?

በአንድ መለስተኛ የገበሬ ጎጆ ቤት ዉስጥ የሚኖሩ ሶሰት የተለያዩ የቤት እንስሳቶች (አንድ ዶሮ፣ አንድ አሳማና አንድ ላም) ስብሰባ ላይ ተቀምጠዋል ። ዋናዉ የተሰበሰቡበት ምክንያት ደግሞ ቁጥራቸዉ ትንሽ በመሆኑና ሁሉም አንድ አንድ ብቻ በመሆናቸዉ የሆነ ችግር ወይም አደጋ ቢገጥማቸዉ በተናጥል ለመከላከል ከባድ መሆኑን በማመናቸዉና ይህንኑ አሳሳቢ ችግር እንዴት በጋራ ህብረት ፈጥረዉ መከላከል እንዳለባቸዉ ዉይይት ለማካሄድና የጋራ ስምምነት ላይ ለመድረስ  ነዉ። ሶስቱም ለብዙ ሰአታት ከተከራከሩና ከተጨቃጨቁ በሗላ፣ “ሁሉም  ቤት ዉስጥ የሚደረግን ማንኛዉም እንቅስቃሴ በንቃት መከታተል እንዳለባቸዉና ለሶስታቸዉም አልያም ከሶስታቸዉ ላንዳቸዉ ሊያሰጋ የሚችልን ማንኛዉንም እንቅስቃሴ ሲደረግ ያየ አልያም የሰማ አካል ለሌሎች የቡድኑ አባላት በፍጥነት ማሳወቅ እንዳለበትና ችግሩ በተከሰተ በአጭር ጊዜ ዉስጥም ሶስቱም አስፈላጊዉን ትብብር በጋራ  በማድረግ  ችግሩን መፍታት እንዳለባቸዉ የሚደነግግ የጋራ ስምምነት ላይ ይደረሳሉ።

Friday, May 18, 2012

ጦር ያዘሉ ግጥሞች

አክሱምን አቃጥሉት!
==================
በስዉር-በስዉር ሳታወጡ ይፋ
አክሱምን አቃጥሉት ላሊበላም ይጥፋ!
ሁሉም ቢተባበር የሚያቅት አ’ደለም
ጢያና ጀጎልን ባንድ ላይ ለማዉደም
መስጅድ፣ ቅርሳ ቅርሱ፣ ፍልፍል ቤተ-መቅደስ
በዘዴ-በዘዴ በየተራ ይፍረስ 
የጥበብ መጸሐፍት ጥንታዊ ብራና
በእሳት ይቀጣጠል ጋዝ ይርከፍከፍና!!
የአያቶቹ ጥበብ ደብዛዉ የጠፋበት
ለምን ይኸ ትዉልድ ወቀሳ ይብዛበት?

Monday, May 14, 2012

እሺ! ይኸንስ የሞት ብድር ማን ይክፈለዉ?

ጎንደር-ጋይንት                                             
1970፣ እሁድ፣ ከጧቱ 4፡10
ከአጭር ጊዜ የስራ ቆይታ በሗላ ክፍለ ሀገር ወደሚኖሩት ቤተሰቦቹ በቅርቡ የተመለሰዉ ታዘበ ወልዴ፣ እንደ አረንጓዴ ስጋጃ ተዘርግቶ በተንጣለለ ትልቅ ግቢ መስክ ላይ ብርኩማ ላይ ተቀምጦ የጧት ፀሀይ እየሞቀ ነዉ። ታዘበ ከብዙ ጊዜ ድካምና ልፋት በሗላ ከአድስ አበባ ዩንቨርሲቲ በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቆ እዛዉ አድድስ አባባ ዉሰጥ የሚገኝ አንድ የመንግስት ከፈተኛ መስሪያ ቤት ዉስጥ ተቀጥሮ መስራት ከጀመረ ገና ስድስት ወሩ ነዉ። የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ በመሆኑና ቤተሰቦቹ ተምሮ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከነበራቸዉ ፅኑ ፍላጎት የተነሳ ብዙ መስዋዕትነትን በመክፈል ነበር አስተምረዉ ለዚህ ደረጃ ያበቁት። በተለይ እናቱ የወርቅዉሀ ታደሰ የእሱ ተከታይ የሆነችዉን ሴት ልጃቸዉን አመለወርቅ ወልዴን በጀርባቸዉ አዝለዉ፣ በአንድ እጃቸዉ የዉሀ መቅጃ በሌላ እጃቸዉ ደግሞ የከብቶች መመለሻ ዱላ ጨብጠዉ፣ ከሁሉም በላይ ላይ ደግሞ ፋታ የማይሰጠዉን የቤት ዉስጥ ስራ አንድም ቀን ደከመኝና ሰለቸኝ ሳይሉ ያለ ማንም አጋዥ ብቻቸዉን እየማሰኑ ነበር አስተምረዉ እዚህ ያደረሱት። አባቱ ወልዴ ታፈረም ቢሆኑ፣ በደከመ ጉልበታቸዉ ብቻቸዉን ሞፈርና ቀንበር እየተሸከሙ፣ ከደረቀ መሬት ጋር እየታገሉና ከአመት አመት እያመረቱ፣ ለልጃቸዉ የሚሆን በቂ የትምህርት ጊዜን አንድም ቀን ሳያጓድሉ ነዉ አስተምረዉ ዛሬ ላለበት ደረጃ ያበቁት። 
የዚህን ፋይል የፒዲኤፍ (PDF) ቅጅ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!

Saturday, May 12, 2012

የኢቲቪ ነገር!

“ኢቲቪ” አድማጭ ተመልካቾቹን ለ“ቲቢ” በሽታ እንደሚያጋልጥ መሐመድ ሰልማን በቅርቡ ባሳተመ መፀሐፉ ደርሸበታለሁ ብሎናል።   እንዴት? ደግሞ፣  “ሴት አያቴ ኢቲቪን ስትመለከትና የማይመስል ነገር ስትሰማ ያስላታል፤ እናም ኢቲቪ ሳምባዋን ሳይነካት አይቀርም”  በማለት ምልክቱንና ምክንያቱን ያብራራልዎታል። ለወንድ አያቴም ቢሆን የጨጓራ ህምም መነሾ ሆኗል ሲልም መሐመድ ኢቲቪን ይወቅሳል።  “ኢቲቪ” ግን በመሐመድ ሴት አያና ወንድ አያ ብቻ አላቆመም፣  አሁን አሁን ሁላችንንም እያሳለን ነዉ። እኔማ ብሶብኛል!  ቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳረጋገጠዉ ከሆነ ደግሞ የሀገር ዉስጥ ዜናዎችና ልማታዊ የቅኝት ፕሮግራሞች የበሽታዉ አይነተኛ ተሸካሚ ቫይረሶች በመሆናቸዉ ቴሌቪዠ በመዝጋትና እነዚህ ፕሮግራሞ ከማየትም ሆነ ከመስማት በመቆጠብ የበበሽታዉን ዘጠና በመቶ ስርጭት ት እንደሚቻል አረጋግጫለሁ ብሏል

Thursday, May 10, 2012

ማራኪ ገጾች


በኤርትራ የወታደሩን ትግል ፈር ያስያዙትና የሚያንቀሳቅሱት እነ ነሲቡ ታዬ ነበሩ። ፍስሐ ደስታ አጋፋሪ ነዉ። ከአብዮቱ በፊት ፖለቲካ ዉስጥ ብዙ የማይገባ ሰዉ ቢሆንም ከማንም ያላነሰ አስተዋፆ አድርጓል። ነገሩ ሁሉ እየጋለ መጥቶ ዉጥረት በበዛብኝ ወቅት አንዳንድ ቀልዶችን በመናገር ፊቴን የሚያፈካዉ ሰዉ ነበረ። ለአስተባባሪ ኮሚቴ “ደርግ” የሚለዉን ስያሜ የሰጠዉ ናደዉ ዘካሪያስ ነዉ።“ [1] ሌተናል ኰሌኔል መንግስቱ ሀይለማሪያም
-----------------------
[1]: ምንጭ፡ ገነት አየለ አንበሴ -የሌተናል ኰሎኔል መንግስቱ ሀይለማሪያም ትዝታዎች ቁ.1 መጽሐፍ

“<<ደርግ>> የሚለዉ ቃል  <<ደረገ>> ከሚለዉ የግዕዝ ግስ የመጣ/ የተወረሰ ነዉ። አድስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ሲተረጉመዉ “ደረገ” ተስማማ ገጠመ አንድ ሆነ  <<አበረ>> በማለት የደስታ ተክለ ወልድ መዝገበ ቃላት ገልፆታል። ይሁን እንጅ ቃሉ የቆየ ቢሆንም በገጠር በኩል እስከ ተወሰነ አመታት ድረስ በተለይ አረሶ አደሩ “ደርግ” የሚለዉን ቃል ትርጉሙ ገብቶት ነበር ለማለት ይቸግራል። ለምሳሌ አንዳንዶች ደርግ ለማለት የሚበረግግ፣ ቀንድ ያለዉ፣ የሚዋጋ፣ መያዣ መጨበጫ የሌለዉ፣ የሚያስፈራ የሚያስበረግግ ወዘተ በማለት ይተረጉሙት ነበር። እንዲያዉም አንዳንዶች ደርግን የሰዎች ማስፈራሪያ እያደረጉ አንድን ህፃን/ልጅ ለማስደንገጥ ሲሉ አዋ! ደርግ መጣ የሚሉ ተደምጠዋል።” [2] ታክሎ ተሾመ
----------------------
[2]: ምንጭ፡ ታክሎ ተሾመ - የደም ዘመን



------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

Monday, May 7, 2012

የታፈኑ (banned) የተደረጉ ድረ-ገጾችን እንደት መመልከት ይቻላል?


በአለም ላይ ካሉ ሀገሮች ሁሉ እጅግ በተራቀቀ መንገድ የተለያዩ የመረጃ ምንጮችን በማፈንና ድረ-ገጾችን በማገድ ቻይናን የሚስተካከላት ሀገር እስካሁን ድረስ አልተገኘም። ከሁልም የሚገርመዉ ደግሞ የሀገሪቱ መንግስት ድረ-ገጾችንና ሌሎች ተዛማጅ የመረጃ ምንጮችን በማፈን (በመከልከል) ብቻ አያቆምም  ከዚህ ይልቅ ታች ድረስ በመዉረድ እያንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋ ምን ምን አይነት ድረ-ገጾችንና የመረጃ ምንጮችን በቀን ዉስጥ እንደጎበኘ የተጠናከረ ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋል። በዚሁ ያልተገባ አካሄድ የተነሳም ከሀገር ዉጭ ከሚኖሩ ቡድኖች ጋር ያልተገባ ግኑኝነት አድርጋችሗል፣ አየር ላይ (online) በተሰበሰበ አስተያየት (petition) ተሳትፋችሗል ፣ ተሀድሶ ይደረግ፣ ሙስና ይቁም በማለት ቅስቀሳ አካሂዳችሗል በሚሉና እና በሌሎች ተመሳሳይ ምክንያቶች ለእስርና እንግልት የሚዳረጉ የጋዜጠኞችና ግለሰቦች ቁጥር የትየሌሌ እንደሆነ  አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ያወጣዉ መግለጫ ያመለክታል። ኢራን፣ ሳዉዲ አረቢያ፣ ቱርክ፣ እና ብራዚል ደግሞ ከቻይና በመቀጠል በተለያዬ መጠንና ስፋት ተመሳሳይ የኢንተርኔት አጠቃቀም እገዳን በሀገራቸዉ ዜጎች ላይ በመጣል  በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ሌሎች ሀገሮች ተርታ ይመደባሉ።
የፍይሉን የፒድኤፍ ቅጅ ለመመልከት እዚህ ይጫኑ

Sunday, May 6, 2012

አንድ ሀገር አንድ ህዝብ ጦማር አፈና ተደረገባት!

አየር ላይ በዋለች 5 ቀን ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ብቻ ከ450 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ከተለያየ ሀገር የጎበኟትና የተለያዬ ባህል፣ ቋንቋና እምነት ባላቸዉ አምስት ግለሰቦች የጋራ ትብብር  የተመሰረተችዉ፣ “አንድ ሀገር አንድ ህዝብ” ጦማር በዚህ ሰአት ኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉ ወዳጆጃችን እንዳይከታተሏት አፈና እንደተደረገባት ተገልጾልናል። ጦማራችን በዘርፈ-ብዙ ሀገራዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ግለሰባዊ ምልከታዎች ማቅረብ ጀምራ የነበረች ሲሆን ከነዚህ በተጨማሪ በሌሎች በርካታ ኪነጥበባዊ፣ ሐይማኖታዊ፣ ፍልስፍናዊ፣ እና ስነ-ጽሁፋዊ ስራዎችና እሳቤዎችም ተጨማሪ ግንዛቤዎችን ለማስጨበጥ ደፍ ቀና በማለት ላይ ባለችበት በዚህ ሰዓት የኢንሳ (INSA) ሰለባ መሆኗ ቢያሳዝነንም እዉነትን በማፈን አልያም ወደ ዉሸት bመቀየር መደበቅ/ማጥፋት/ እንደማይቻል ለአፈኞቻችን ለመግለጽ እንዎዳለን። 

Saturday, May 5, 2012

ሚያዚያ 27-የድል በአል


“ይህ የምትሰሙት ድምጽ የኔ የንጉሳችሁ የቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ ነዉ። አባቶቻችን ደማቸዉን አፍሰዉ ዐጥንታቸዉን ከስክሰዉ በነፃነት ያቆዩልን አገራችንን ወደ ከፍተኛዉ የሥልጣኔ ደረጃ ለማራመድ የምንደክምበት ጊዜ ከጥንት ዠምሮ ስለሆነ ደመኛ ጠላታችን ኢጣሊያ ይህንን እይታ ወሰናችንን ጥሳ የግፍ ጦርነት እንዳደረገችብን ሁላችሁም የምታዉቁት ነዉ። እኛም በተቻለን ከተከላከልን በሗላ ርዳታ ለመጠየቅ ወደ መንግስታት ማሕበር ወደ ወዳጆቻችን መንግስታቶች መጣን እዚህ ስንነጋገር በቆዬንበት  ጊዜ የኢትዮጵያ አርበኞች ሰይፋችሁን ሳትከቱ ፊታችሁን ሳትመልሱ ሰንደቅ ዐላማችሁን ሳታጥፉ ለባዕድ አንገዛም በማለት በመሳሪያ ብዛት ከሚበልጣችሁ ጨካኝ ጠላት ጋር የባሕርይ የሆነዉን ዠግንነታችሁን መሣሪያ አድርጋችሁ  በኢትዮጵያ አምላክ ብቻ ተማምናችሁ በዠግንነት ቀንና ሌሊት በዱር በገደል ስትጋደሉ ቆይታችሁ ይኸዉ አሁን እንደምታዩት የማያቋርጥ የአምስት አመት ትግላችሁ የድካማችሁንና የመሥዕዋታችሁን ፍሬ ለማየት እንድትበቁ አደረጋችሁ።

የዋልድባ ገዳም ዝርፊያ ተፈፀመበት

የዋልድባ ገዳም በአምስት መሳሪያ ታጠቁ ፊታቸዉን የተሸፋፈኑ ግልሰቦች 66 ሺ ብር እንደተዘረፈ ምንጮች ጠቆሙ፡፡ ባለፈዉ ማክሰኞ ሌሊት ወደ ገዳሚ ገብዉ ዝርፊያ ፈፅሟል የተባሉት ግለሰቦች ወደ ቦታዉ ሲደርሱ ክላሽንኮቭ መሳሪያቸዉን በመጠቀም በገዳሙ የሚገኙትን መነኮሳት በአንድ ክፈል ከቆለፉ በሓላ ዝርፊያዉን እንዳከናወኑ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ዘራፊዎቹ በቤተ እግዚያብሔር ዙሪያ የሚገኙትንና የተቆለፉትን ግማጃ ቤቶች፣ የነዋዬ ቅዱሳት ማስቀመጫ እቃ ቤትና የእህል ጎተራዎችን ሰብረዉ በመግባት 66ሺ ብር ከማስዳቸዉም በላይ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶችን በመበታተን በእቃዎቹ ላይ ጉዳት እንዳደረሱ ተገልፃል::   /አድስ አድማስ ጋዜጣ-ሚያዚያ 27-2004/



------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

ሌብኒትዝ

ጎትፍሪድ ቪልሄልም ሌብኒትዝ (July 1 (June 21 OS) 1646 – November 14 1716 እ.ኤ.አ.) የ17ኛው ክፍለ ዘመን የጀርመን የሒሳብ ሊቅ፣ ሳይንቲስት፣ ፈላስፋ፣ ፍርድ አጥኝና ባጠቃላይ መልኩ ሁለ ገብ ተመራማሪ ነበር። ሌብኒዝ ከኢሳቅ ኒውተን ትይዩ ካልኩለስ የተባለውን የዕውቀት ዘርፍ ፈጥሯል። አሁን ድረስ ተማሪወች የሚጠቀሙበት የካልኩለስ የአጻጻፍ ስልት በዚህ ሰው የተፈለሰፈ ነው። ለኮምፒዩተር ስራ እጅግ ወሳኝ የሆነውን የሁለትዮሽ ቁጥር ስርዓት (ባይናሪ ቁጥር) ዘመናዊ ኮምፒዩተሮች ከመሰራታቸው 300 አመት በፊት ፈልስፏል።

በፍልስፍናው ዘርፍም ጠለቅ ያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የሌብኒዝ ፍልስፍና እንደ ደካርት ፍልስፍና ቀልበኛ ይባላል። «ይህ ዓለም እግዚአብሔር ሊፈጥራቸው ይችላቸው ከነበሩ ዓለማት ሁሉ የተሻለ» ነው የሚለው ድምዳሜው የሌብኒዝን ፍልስፍና ብሩህ ተስፈኛ በሚባል መደብ ስር እንዲታወቅ አድርጎታል። የሌብኒዝ ፍልስፍና የቀደምት አውሮጳውያን የፍልስፍና ዘዴ ተብሎ የሚታወቀውን ስኮላስቲክ ወደ ኋላ የሚመለከትና ወደፊት ደግሞ በ20ኛው ክ/ዘመን ብቅ ያሉን ዘመናዊ ሥነ አምክንዮ እና ትንታኔአዊ ፍልስፍናን የተነበየ ነበር። በርግጥም ከደካርትና ከስፒኖዛ ጋር በመሆን ሌብኒዝ የ17ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮጳ ዋና ቀልበኛ ፈላስፋ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።

Friday, May 4, 2012

ዓፄ ቴዎድሮስ

ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ (ጥር ፮ ቀን ፲፰፻፲፩ ዓ.ም. - ሚያዝያ ፮ ቀን፲፰፻፷ ዓ.ም.) ከ፲፰፻፵፯ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታችው ድረስ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበሩ። በትውልድ ስማቸው ካሳ ሃይሉ ሲባሉ፣ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፣ በወታደራዊ ስማቸው መይሳው ካሳ እና እንዲሁም አንድ ለናቱ ተብለው የሚታወቁ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ወታደርና ፖለቲከኛ ነበሩ።

ቴዎድሮስ ጥር ፮ ቀን ፲፰፻፲፩ ዓ.ም. ሻርጌ በተባለ ቦታ ቋራ ውስጥ፣ ከጎንደር ከተማ በስተ ምዕራብ ተወለዱ። የተወለዱትም አገሪቷ በባላባቶች ተከፋፍላ በምትመራበት-ዘመነ መሳፍንት በሚባለው ወቅት ነበር። አባታቸው ደጃዝማች ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ የቋራ ገዢ ነበሩ። ዓፄ ቴዎድሮስ በህጻንነታቸው የቄስ ትምህርት ከቀሰሙ በኋላ፣ የአጎታቸውንና በኋላም ለጥቂት ጊዜ የጎጃሙን ጦር መሪ የጎሹ ዘውዴን ጦር ተቀላቀሉ። በዚሁ የውትድርና ዘመናቸው ከፍተኛ ችሎታን ማስመዝገብ ስለጀመሩና ዝናቸው ስለተስፋፋ በ፲፰፻፴፱ ዓ.ም. በወይዘሮ መነን ሊበን አምዴ አነሳሽነት የልጇን የራስአሊ አሉላን ልጅ፣ ተዋበች አሊን ተዳሩ ፤ እንዲሁም በደጃዝማችነት ማዕረግ የቋራ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ። ቴዎድሮስ ግን በ፲፰፻፵፬ ዓ.ም. አጠቃላይ የዘመነ መሳፍንት ሥርዓትን በመቃወም በሰሜናዊ ባላባቶች ላይ ዘመቻ ጀመሩ።

መንግሥቱ ንዋይ

መንግሥቱ ንዋይ በ፲፱፻፰ ዓ/ም አዲስ አበባ ላይ አራዳ ጊዮርጊስ ገዳም ሠፈር አካባቢ ተወለዱ። አባታቸው ዓለቃ ንዋይ የደብሩ ዓለቃ ነበሩ። ትምሕርታቸውን በተፈሪ መኮንን ትምሕርት ቤት ተከታትለው አዲሱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ሲመሰረት ወደዚያ ተዛውሩ። የገነት ጦር ትምሕርት ቤት ሲከፈት ደግሞ፣ መንግሥቱ ንዋይ ተመልምለው ከገቡት ዕጩ መኮንኖች አንዱ ነበሩ። ሌሎች (በኋላ ጄነራሎች) እንደነ አቢይ አበበ፣ አሰፋ አያና፣ ኢሳያስ ገብረሥላሴና ከበደ ገብሬ በዚሁ ትምሕርት ቤት ከመንግሥቱ ጋር የነበሩ ዕጩ መኮንኖች ናቸው።
መንግሥቱ ከዚያው የጦር ትምሕርት ቤት በመቶ አለቃ ማዕረግ ተመርቀው ሲወጡ ወዲያው የጠላት ኢጣልያ ጦር አገሪቱን ይወርና እሳቸው ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ወደማይጨው ዘምተው ግዴታቸውን ተውጥተዋል። ጠላትም ድሉን ሲቀዳጅ እና ንጉሠ ነገሥቱ ሲሰደዱ መቶ አለቃ መንግሥቱ በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደሸሸበት ነቀምት ሄደው እዚያ “ጥቁር አንበሳ” የሚባለውን ማኅበር መሥራች አባል ናቸው። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ከጓደኞቻቸው ጋር ወደጅቡቲ ተሰደዱ። በ፲፱፻፴፪ ዓ/ም ንጉሠ ነገሥቱ ተመልሰው ካርቱም ሲገቡ እነኚህን ስደተኛ መኮንኖች ከጅቡቲ ወደካርቱም እንዲመጡ ይደረግና መንግሥቱ ንዋይ ከነ ሙሉጌታ ቡሊ፣ ነገሠ ወልደሐና፣ ወልደማርያም ኃይሌ፣ ዘውዴ ገበሳ እና ታምራት ዘገየ ጋር ሆነው ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ተቀላቀሉ። ወዲያውም ከእሳቸው ጋር በ፲፱፻፴፫ ዓ/ም አብረው ወደኢትዮጵያ በድል ሲገቡ በክብር ዘበኛ ውስጥ በጄኔራል ሙሉጌታ ሥር ሻምበል ሆነው ቆዩ። በመስከረም ወር ፲፱፻፵፱ ዓ/ም ኮሎኔል መንግሥቱ ብርጋዴር ጄኔራል ተብለው የክብር ዘበኛ ጠቅላይ አዛዥነትን ተሾሙ። ተራማጅ እና የክብር ዘበኛን ሠራዊት በሰገላዊ ውትድርና ንቃተ ሕሊናውን ለማዳበር ብዙ የጣሩ መኮንን እንደነበሩ ተመስክሮላቸዋል።

------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

ልጄ ሆይ

ልጄ ሆይ በዚህ አለም ሀይለኞች ገንዘብና እዉቀት ሁለቱ ብቻ ናቸዉ። ገንዘብ እና እዉቀት ያለዉ ሰዉ እስከ ጊዜዉ ደስ ብሎት ይኖራል። ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ገንዘባቸዉን በማይረባ ጉዳይና  ሰዉን በማጥፋትና ራሳቸዉን ብቻ ለመጥቀም አድርገዉ ሀይላቸዉ ይደክማል። ገንዘባቸዉን ለንግድና ለድሃ እዉቀታቸዉንም ለስራና ለሰዉ ጥቅም የሚያደርጉ ሰዎች ግን በሀይል ላይ ሀይል እየጨመሩ ይኖራሉ። እነሆ ለዚህ አንድ ምሳሌ እነግርሀለሁ። ነጭ ስንዴ በባለሙያ እጅ ሲሆን ያማረና የጣፈጠ እንጀራ ይሆናል። በባለሙያ እጅ ያልሆነ እንደሆነ ግን እንደ ዘንጋዳ እንጀራ ይሆናል። ገንዘብና እዉቀትም በደግ ሰዉ እጅ ሲገቡ ለመልካም ነገር ይሆናሉ። በክፉ ሰዉ እጅ ሲጉ ግን ለጥፋት ነገር ብቻ ይሆናሉ።

ልጄ ሆይ የምትሰራዉን ስራ ሁሉ ሰዉ ቢያየዉ ቢሰማዉም አይጎዳኝም ብለህ ትሰራዉ እንደሆነ ነዉ እንጅ አይታይብኝም  አይሰማኝብም ብለህ አትስራዉ። አንተ ምንም ተሰዉረህ ብትሰራዉ ከተሰራ በሗላ መታየቱና መሰማቱ አይቀርም። /ብላቴን ህሩይ ወልደ ስላሴ- ወዳጄ ልቤና ሌሎችም/

------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

እምነትና ፍልስፍና

ፍልስፍና በተለያዩ ሰወች የተለያየ ግንዛቤና መረዳት አለው። ሆኖም ከሞላ ጎደል የፍልስፍና ዘርፎችና የሚያነሷቸው ጥያቄዎች እንዲህ ይቀርባሉ፡
ሜታፊዚክስ : እውንነት ምንድን ነው? እውን የሆነ/የሆኑ ምን ነገሮች አሉ? ከምናስተውለው ዓለም ውጭ ሌላ ዓለም አለ?
ሥነ ዕውቀት: አለምን መረዳት እንችላለን? እንዴት ማወቅ እንችላለን? ከራሳችን ውጭ ሌላ ሃሳብ እንዳለ እንዴት እናውቃለን?
ሥነ ምግባር: ሰናይና ዕኩይ (ጥሩና መጥፎ) ልዩነት አላቸው? ካላቸው እንዴት ልንለያቸው እንችላለን? ምን አይነት ምግባር ሰናይ (ጥሩ) ነው? ለአንድ ምግባር ዋጋ ለመስጠት የዋጋ ስርዓት መኖር አለበት፣ ይህ የዋጋ ስርዓት ከየት ይመነጫል? ከአምላክ? ወይስ ከየት? አንድ ምግባር ፍጹም ጥሩ ወይም ፍጹም መጥፎ ሊባል ይችላል? የራበው ሰው ቢሰርቅ ስርቆቱ ዕኩይ ነው? ወይንስ ሥነ ምግባር አንጻራዊ ነው? እንዴት ህይወቴን መምራት አለብኝ? ሁላችንስ እንዴት እንኑር?
ሥነ አምክንዮ፡ ትክክለኛ ሃሳብ እንዴት እናመነጫለን? አንድ ሃሳብ ስሜት የማይሰጥ መሆኑን እንዴት ማወቅ እችላለሁ? የክርክርን አሸናፊ እንዴት መለየት ይቻላል?
ሥነ ውበት፡ ኪነት ምንድን ነው? ውበት ምንድን ነው? የውበት ቋሚ መስፈርት አለው? ኪነት መስፈርቱ ነው? እንግዲያስ የውበት ትርጉሙ ምንድን ነው? የኪነት አላማ ምንድን ነው? ኪነት እኛን እንዴት ይነካናል?ኪነት ዕኩይ ሊሆን ይችላል?ኪነት የህብረተሰብን ኑሮ ይሸረሽራል ወይስ ያሻሽላል? አንድ ከዋኝ የሚሰራውን ያውቃል? ለምሳሌ ድራማ ላይ ፕሬዜዳንት የሆነ ከዋኒ ዕውን ፕሬዜዳንት ሆኖ ሊሰራ ይችላል? የኪነት ተግባር የውኑን አለም መኮረጅ ነው? በመኮረጁ የቱን ያክል ነባራዊውን አለም ያጣምማል?

------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

የማኪያቶ ወግ

ጌሾ በአፍሪካ ብቻ የሚበቅል በተለይ በኢትዮጵያና በደቡብ አፍሪካ የሚገኝ ተክል ነው። በኢትዮጵያ ጠላና ለጠጅ ሲጠመቅ ጌሻ ይገባል። የሚበቅለውም ከባህር ወለል በላይ 1400-3200 ሜትር ላይ ነው። ቆረቆርና ሌሎች የፈንገስ በሽታወችን በደቀቀ ፍሬውና ቅጠሉ በመቀባት ለማዳን ይቻላል ህጻናት እንጥላቸው ከተቆረጠ በኋላ ህመማቸውን ለማስታገስ አፋቸው ውስጥ የጌሾ ቅጠል ይደረጋል ቂጥኝ በሽታን ለመከላከል ሆድ ድርቀት ለማስወገድ ሥሩ ደምን ለማጥራት ያገለግላል:: የጌሾ ግንድ በጣም ጠንካራ ስለሆነ ለተለያዩ የእንጨት ውጤቶች ሊያገለግል ይችላል። የጌሾ ዛፍ በምንጮች አካባቢ ቢተከል የመሬት መሸርሸርን ሊከላከል ይችላል። ከእርሻ ማሳ ዳርቻ ላይ በመትከልም የመሬትን ንጥር ነገር ከነፋስ እና ከዝናብ መከላከል ይቻላል። የጌሾ አበቦች በንቦች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ስላላቸው የጌሾ ተክል ለንብ እርባታና ለማር ምርት ከፍተኛ ግልጋሎት ሊሰጥ ይችላል።

------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

ሰምናወርቅ


ለሰዎችን እምቅ መልዕክት ለማስተላለፍና ግንዛቤ ለማስጨበጥ ከሚረዱን የስነ-ጽሁፍ ስራዎች መካካል ስነ-ግጥም የመጀመሪያዊና ምናልባትም አቻ የማይገኝለት ነዉ ብንል ማጋነን አይሆንም። ኢትዮጵያ ሀገራችንም በተለያዬ ጊዜ ስሟን ያስጠሯት የበረካታ ባለቅኔዎች እናት እንደመሆኗ መጠን በተለያዩ ባለቅኔዎች የተጻፉና የተሻለ መልእክት አላቸዉ የምንላቸዉ የስነ-ግጥም ስራዎች በዚህ አምድ ስር ይስተናገዳሉ። እገረመንገዳችንንም እነዝህኑ የስነ-ጽሁፍ ባለዉለታዎቻችንን እንዘክራለን።

------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

ሀገር ማለት

ሀገራችን ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የረጅም ዘመን የታሪክና የባህል መሰረቶች ያሏት ሀገር ብትሆንም ዛሬ ዛሬ  የምራባዊያንን አኗኗርና አስተሳሰብ አንጋጠን በመመልከትና ያሉንን ባህላዊና ሀገራዊ እሴቶችን አንድም ባለ ማስተዋል አንድም ሗላቀር አድርጎ በመሆሰድ ምስኪን ልጆቿ “አባቱን አያዉቅ አያቱን ይናፍቃል” እንዲሉ በማያገባንና በመማይመለከተን የምዕራባዊና አስተሳሰብ ተጠልፈን ለመዉደቅ እየታተርን እንገኛልን።  አገር ማለት ይለናል ታሪክና ምሳሌ 3ኛ መጸሐፍ … “አገር ማለት በታሪክ በቋንቋ በሀይማኖት፣ በልምድ፣ በተስፋ፣ በደስታና በመክራ ተሳስሮ የሚኖር አንድ ወገን የሆነ ሕዝብ የሚኖርበት የዓለም ክፍል ነው። እግዚአብሔር ከምድርዋ ፍሬ ሕይወት እንዲገኝባት በማድረጉ፤ አገር እያጠባች የምታሳድግ ፍቅርዋ በአጥንትና በሥጋ ገብቶ የማይደመሰስ፣ እናት ማለት ነው። አገር አባት፣ እናት፣ ዘመድ፣ ምግብ ፣ጌጥና ሀብት በመሆኑ፤ ድህንትና ጥቃት በመጣ ቁጥር እስከ ሞት ድረስ እንዲሠራበት ከአያት ከቅድም አያትና ከአባቶች በጥብቅ የተሰጠ ያደራ ገንዘብ ነው”። 

ማራኪ ገጾች

ማንበብ ሙሉ ሰዉ ያደርጋል የሚል አንድ የቆዬ አባባል አለ። በርግጥም ማንበብ ሙሉ ሰዉ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ሀገርና ሙሉ ተስፋ እንዲኖረን በማድረግ የተሻለ ትዉልድ እንዲፈጠር ያደርጋል። ነገር ግን ኢትዮጵያኖች ብሎም አፍሪካኖች የማንበብ ባህላችን ገና ያልዳበረና “አፍሪካዊያን እንዳያዉቁት የምትፈልገዉን ሚስጥር መጸሐፍ ዉስጥ ደብቀዉ” ተብሎ እስከሚሳለቅብን ድረስ ሗላ ቀር እንደሆነ ለማንም የተሰዎረ ሀቅ አይደለም። አንድ መጽሔት የአፍሪካ ምሑራን አንድ ጊዜ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ ስለማያነቡ ወደ መሐይምነት ይቀየራሉ በማለት ነበር የገለጻቸዉ፡፡ ነገር ግን ዲግሪ ለተወሰነ የትምህርት ዘርፍ የሚሰጠ ማስረጃ እንደመሆኑ መጠን፣ ምሑራንም ሆኑ ማንኛውም ሰው ማንበብ ይገባዋል፡፡ ይህም ተምሮ ከማያነብ ሰነፍ ይልቅ ባለመማሩ የማያነብ መሐይም የተሻለ ተስፋ አለዉና ነዉ። በመሆኑም የዚህ አምድ ዋና አላማ ከተለያዩ መጸሐፍቶች ገጽ  ላይ ሰዎችን ለተጨማሪ ንባብ ይኮረኩራሉ ያልናቸዉን ጥቂት አንቀጾችን (በመዉሰድ) በመዉሰድና ለንባብ በማቅረብ የተሻለ የማንበብ ባህል እንዲኖረን ለሚደረገዉ ጥረት የራሱን አስተዋጾ ማበርከት ነዉ።

------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

Tuesday, May 1, 2012

አንድ ህዝብ አንድ ሀገር

ይህ የጡመራ ድረ-ገፅ (Blog) በዋናነት የተለያየ እምነት፣ ባህልና  ቋንቋ  ያላቸዉ አምስት ግለሰቦች በጋራ የሚጦምሩበት መድረክ ነዉ። በመሆኑም በዘርፈ-ብዙ ሀገራዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ግለሰባዊ ምልከታዎች የሚቀርቡበት ሲሆን ሌሎች በርካታ ኪነጥበባዊ፣ ሐይማኖታዊ፣ ፍልስፍናዊ፣ እና ስነ-ጽሁፋዊ ስራዎችና እሳቤዎችም ይስተናገዱበታል። በአንድ ሀገር ዉስጥ የሚኖር ሕዝብ ምንም እንኳን የተለያዬ እምነት፣ባህልና ቋንቋ ተከተይና ባለቤት የሆኑ ግለሰቦች ጥርቅም መሆኑ እሙን ቢሆንም ከነዚህና  ከሌሎች ተጨማሪ  ልዩነቶች ባሻገር ሌሎች በርካታ ለድርድር የማይቀርቡ የጋራ ሀገራዊ ጉዳዮችም ሊኖሯቸዉ እንደሚገባ /እንዳሉዋቸዉ/ ሌላዉ የማይካድ ሀቅ ነዉ። ነገር ግን ይህንን በልዩነት ዉስጥ ያለን ሀገራዊ አንድነት ለአደጋ የሚያጋልጡ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ከሁሉም በላይ ግን በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለዉ ጉዳይ ዜጎች ካሉዋቸዉ የጋራ አንድነቶች ይልቅ ባሏቸዉ ጥቃቅን ልዩነቶች ላይ ብቻ የማተኮር አዝማሚያና በዚህም ምክንያት የዘረኝነትና የጎሰኝነት መንፈስ በማስፋፋት ለአምባገነን ገዢዎች ስልጣን ማራዘሚያና መጠቀሚያ የመሆብ ሰለባ ነዉ።  ማንም ይህንኑ እዉነታ መሰረት አድር ሀገራችንን ኢትዮጵያን ያለቸበትን ሁኔአታ ቢመረምር በግምባር ቀደምትነት ሊጋፈጣቸዉ ሚችላቸዉ በርካታ እዉነታዎች መካከል ከቅርብ ጊዜ ወድህ  እየተስተዋለ የመጣዉን የዘረኝነትና የመከፋፈል አደጋዎች ይሆናል። ይህንንም ጉዳይ   ልብ ብሎ ላስተዋለ ማንኛዉም ሰዉ ወዴት እያመራን እንደሆነ ለመገመት ነብይነትን የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም።