Monday, May 7, 2012

የታፈኑ (banned) የተደረጉ ድረ-ገጾችን እንደት መመልከት ይቻላል?


በአለም ላይ ካሉ ሀገሮች ሁሉ እጅግ በተራቀቀ መንገድ የተለያዩ የመረጃ ምንጮችን በማፈንና ድረ-ገጾችን በማገድ ቻይናን የሚስተካከላት ሀገር እስካሁን ድረስ አልተገኘም። ከሁልም የሚገርመዉ ደግሞ የሀገሪቱ መንግስት ድረ-ገጾችንና ሌሎች ተዛማጅ የመረጃ ምንጮችን በማፈን (በመከልከል) ብቻ አያቆምም  ከዚህ ይልቅ ታች ድረስ በመዉረድ እያንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋ ምን ምን አይነት ድረ-ገጾችንና የመረጃ ምንጮችን በቀን ዉስጥ እንደጎበኘ የተጠናከረ ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋል። በዚሁ ያልተገባ አካሄድ የተነሳም ከሀገር ዉጭ ከሚኖሩ ቡድኖች ጋር ያልተገባ ግኑኝነት አድርጋችሗል፣ አየር ላይ (online) በተሰበሰበ አስተያየት (petition) ተሳትፋችሗል ፣ ተሀድሶ ይደረግ፣ ሙስና ይቁም በማለት ቅስቀሳ አካሂዳችሗል በሚሉና እና በሌሎች ተመሳሳይ ምክንያቶች ለእስርና እንግልት የሚዳረጉ የጋዜጠኞችና ግለሰቦች ቁጥር የትየሌሌ እንደሆነ  አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ያወጣዉ መግለጫ ያመለክታል። ኢራን፣ ሳዉዲ አረቢያ፣ ቱርክ፣ እና ብራዚል ደግሞ ከቻይና በመቀጠል በተለያዬ መጠንና ስፋት ተመሳሳይ የኢንተርኔት አጠቃቀም እገዳን በሀገራቸዉ ዜጎች ላይ በመጣል  በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ሌሎች ሀገሮች ተርታ ይመደባሉ።
የፍይሉን የፒድኤፍ ቅጅ ለመመልከት እዚህ ይጫኑ


ዳግማዊ ቻይና የሆነችዉ ሀገራችን ኢትዮጵያም በኢንሳ (INSA) ወሮበሎች በኩል በመታገዝ መረጃን በማፈንና ድረ-ገጾችን በማገዱ ረገድ እያሳየችዉ ያለዉ  እመርታ ይበል የሚያሰኝ ሲሆን አንድ ሰዉ ለአንድ ድረ-ገጽ የተመደበ በሚመስል መልኩ ነባርና አዳድድስ የሚከፈቱ ድረ-ገጾችንና የጡመራ መድረኮችን ሪከርድ ሊባል በሚችል ፍጥነት ከስር ከስር እየተከታተሉ በመዝጋት ወደር አልተገኘላቸዉም። መቸም በዚህ ፍጥነትና ትጋት የሚቀጥሉ ከሆነ እንኳንስ የተከፈቱትንና አየር ላይ የዋሉትን ይቅርና ገና ለመከፈት በሰዉ ልብ ዉስጥ ያሉትን ድረ-ገፆችን ጭምር ቀድመዉ በመዝጋት የአፈና ስልት መምህራቸዉ የሆነችዉን ቻይናን ሳይቀር በመቅደምና ከአለም አንደኛ በመሆን በቅርቡ እንደሚያስደምሙን ጥርጥር የለዉም። 

ያም አለ ይህ ግን  “ከአንጀት ካዘኑ እምባ አይገድም!” እንደሉ የዚህ አይነት የመረጃ ክልከላዎችንና እገዳዎች በተጣለባቸዉ ሀገሮች የሚኖሩ በርካታ ዜጎች የተለያዩ ዘዴዎችንና የቴክኖሎጅ አማራጮችን በመጠቀም ያለባቸዉን የመረጃ ረሀብ ሳያስታግሱ  ዉለዉ አያድሩም። በዚህም አሁን ባለንበት ዘመን መረጃን የሚፈልግን ሰዉ የሚፈልገዉን መረጃ በማፈን አልያም እንዳይታይ በመከልከል ግለሰቡ እንዳይመረጅ ማድረግ ፈጽሞ እንደማይቻል በተደጋጋሚ በተግባር አሳይተዉናል። እኛም ሰሞኑን የዚሁ የመታገድ ሰለባ  የሆነችዉን “አንድ ሕዝብ አንድ ሀገር” የጡመራ ድረ-ገጽንና ሌሎች ተመሳሳይ እጣ ፈንታ የገጠማቸዉን ድረ-ገጾች የተጣለባቸዉን እገዳ በማለፍ እንደት መከታተልና መረጃን ማግኘት እንደሚቻል አንዳንድ ነጥቦችን ለማለት ወደድን።
በመሰረቱ አምባገነን መንግስታት ከሚጥሏቸዉ ያለተገቡ የመረጃ ማዕቀቦች በተጨማሪ ህጋዊ መንገድን ተከትለዉ የሚጣሉ ሌሎች በርካታ የኢንተርኔት (ድረ-ገጽ) አጠቃቀም እገዳዎች እንዳሉ ልብ ማለት ይገባል። ለምሳሌ ያክል፣ የተከለከሉ (ጎጅ) የመረጃ ይዘትን የሚያስተላልፍ ድረገጾች (ለምሳሌ ወሲብ ቀስቃሽ ምስሎችን የያዙና ህገወጥ የዕፅ ዝዉዉር የሚያበረታቱ (የሚያካካሂዱ) ድረ-ገፆች)፣ የኮፕራይት ህግን ሳይጠብቁ የሌሎች ግለሰቦች (ተቋማት) ስራዎችን የራሳቸዉ በማሰመሰል ገቢን የሚሰበስቡ አልያም የሚያሰራጩ የኢንተርኔት ገጾች፣  ሽብርተኝነትን የማስፋፋትና የማራመድ አላማና ይዘት ያላቸዉ ድረ-ገጾች፣ የግል ወይም የተቋማትን ኮምፒዉተሮች ያለፍቃድ ሰብሮ በመግባት፣ የዳታ/መረጃ ማከማቻዎች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ፣ መረጃን የመስረቅ፣ የማጥፋት ወይም የመቀየር ሙከራን የሚካሂዱና ያልተገቡ የኮምፒዉተር ፕሮግራሞችን (computer virus) የሚያሰራጩ ድረ-ገጾች፣ ዘረኝነትንና የአንድ ሐይማኖት የበላይነትን በመስበክና በማስተጋባት አንድ ወገን (ህዝብ) በሌላ ወገን (ህዝብ) ላይ ያልተገባ ትንኮሳና ጥቃት እንዲያደርስ የሚገፋፉና ሌሎች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸዉን መረጃዎች የያዙ (የሚያራምዱ) ድረ-ገጾችና የመረጃ ምንጮች የተለያዩ አለማቀፋዊ እና ሀገራዊ ህጎችን መሰረት በማድረግ ሊከለከሉ (ሊታገዱ) ይችላሉ። 

ይህም  ከተለያዩ ግለሰቦች (ተቋማት) የሚደርሱ ጥቆማዎችን (abuse reports)ና የድረ-ገጽ የግምገማ ዉጤቶችን (website analysis reports) መሰረት በማድረግ  በተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶች (ለምሳሌ Google)፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች (Internet Service Providers ለምሳሌ ኢትዮ-ቴሌ) እና በሌሎች ሀገራዊ የደህንነት ተቋማት (ለምሳሌ INSA) በኩል እገዳዉ ተፈጻሚ ሊደረግ ይችላል። በመሆኑም ከላይ በዝርዝር የተገለጹትን አይነት የይዘት ችግር ያለባቸዉና ሌሎች በአለም አቀፍ ደረጃ የተከለከሉ ተግባራትን የሚያከናዉኑ ድረ-ገጾችንና የመረጃ ምንጮችን ዜጎች ለሀገራዊና ግለሰባዊ ደህንነት ሲባል በተዘዋዋሪም ይሁን በቀጥታ ባይጎበኟቸዉ ይመከራል። በአንዳንድ ሀገሮችም የዚህ አይነት ይዘት ያላቸዉን ድረገጾች ሲጎበኙ (ሲጠቀሙ) የተገኙ ግለሰቦችን በህግ አግባብ የሚቀጡ በመሆኑ ሰዎች በማዎቅም ይሁን ባለማወቅ እነዚህን ህጎች በመተላለፈ ወንጀል ሊከሰሱና ለረጅም ጊዜ እስርና ለሌሎች ተመሳሳይ ቅጣቶች ሊዳረጉ ይችላሉ።

በመሆኑም የዚህ ጽሑፍ ዋና አላማ ባላቸዉ ህገወጥ ይዘት ምክንያት በህጋዊ መንገድ የተከለከሉ ድረ-ገጾችን እንደት መጠቀም እንደሚቻል ማስተማር ሳይሆን ህጋዊ ይዘት ያላቸዉ መልእክቶችን የሚያስተላልፉና ለሰዎች በርካታ ሀገራዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያላቸዉን መረጃዎች የሚያቀብሉ ሆነዉ ሳለ ሆን ተብሎ፣ ዜጎች ተገቢዉን መረጃ እንዳያገኙ በማሰብ በመንግሰት አሊያም በሌሎች ተማሳሳይ ተቋማት በኩል ህጋዊ መንገድን ባልተከተለ መልኩ የታፈኑ ወይም እገዳ የተጣለባቸዉን የመረጃ ድረ-ገጾችን እንደት  መከታተልና መረጃን ማግኘት እንሚቻል  አንዳንድ ግንዛቤዎችን ማስጨበጥ ነዉ። ማንም ሰዉ የተለያዩ የኢንተርኔት አጠቃቀም ክልከላ የተጣለባቸዉን ድረ-ገጾች በርካታ የተለያዩ ዘዴዎችንና የቴክኖሎጅ አማራጮችን በመጠቀም መከታተል (መመልከት) ይቻላል። ሆኖም እነዚህ ቴክኖሎጅዎችንና አማራጮች ከመመልከታችን በፊት፣ የድረ-ገጽ ክልከላ እንደት ተግባረዊ እንደሚደገግ እንደሚከተለዉ በአጭሩ እንመልከት።

በመረጃ መረብ ላይ የሚኖረን ማንኛዉም የመረጃ ፍስት በሁለት መልኩ ከፍሎ መከልከል (ማገድ) ይቻላል ይህም ወደ ዉስጥ የሚገቡ መረጃዎችን በማገድ ወይም ከዉስጥ ወደ ዉጭ የሚወጡ መረጃዎች ላይ እገዳን በመጣል አሊያም ደግሞ ሁለቱንም ተግባራዊ በማድረግ ሊሆን ይችላል። ይህንን በቀላል ምሳሌ ለመረዳት ለምሳሌ አንድን ሀገርን ብንወስድ ከሀገር ዉጭ ካሉ ሌሎች የመረጃ መረቦች (External networks) ሀገር ዉስጥ ወዳሉ የመረጃ መረቦች (internal networks) የሚገቡ አሊያም ከሀገር ዉስጥ የመረጃ መረቦች ወደ ሌሎች ዉጭ ወዳሉ የመረጃ መረቦች (ኔትዎርኮች)  የሚዎጡ (የሚላኩ) የተለያዩ መረጃዎችን ይዘት በቀላሉ ለመከታተል  እንዲረዳና በዋናነትም ለሀገርና ለህዝብ አደገኛ የሆኑ ፕሮገራሞች ሾልከዉ እንዳይገቡና ሀገር ዉስጥ ባሉ የተቋማት(የግለሰብ) ኮምፒዉተሮችና የመረጃ ማከማቻዎች ላይ ጥቃት እንዳያደርሱ፣ ወይም ደግሞ ቀደም ሲል ከላይ በዝርዝር የተመለከትናቸዉን አይነት የተከለከሉ የመረጃ ይዘቶችን የያዙ ድረገ-ጾች ወደ ሀገር ዉስጥ እንዳይገቡና እንዳይታዩ ለመቆጣጠርና ለማገድ እንደ ዋና መግቢያ በር ሆኖ የሚያገለግል ፕሮክሲ ስርቨር የሚባል ኮምፒዉተር ይኖረዋል። ይህም ኮምፒዉተር የራሱ የሆነ የፕሮክሲ አዳራሻና የፖርት ቁጥር (proxy address and port number) የሚሰጠዉ ሲሆን ማንኛዉ ወደ ሀገር ዉስጥ  የሚገባ አሊያም  የሚዎጣ መረጃ በሙሉ በዚሁ ሰርቨር (port number) በኩል ማለፍ የሚኖርበት ሲሆን ይህንን የማያሟላ ማንኛዉ ኮምፒዉተር ግን ከሌላ ከሀገር ዉጭ ካለ ማንኛዉም ሌላ ኮምፒዉተር ጋር ግንኙነት ማድረግ አይችልም (የኢንተርኔት አገልገሎት ማግኘት አይችልም) ማለት ነዉ። 

እንደዚህ ካለና በሀገር ደረጃ ከሚቀመጥ የመቆጣጠሪያ ኮምፒዉተር በተጨማሪም ከፍተኛ የመረጃ ፍስት ያላቸዉ ሌሎች ተቋማትና ድርጅቶችም(ለምሳሌ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የደህንነት መስሪያ ቤቶች፣ ባንኮች ወዘተ) የራሳቸዉ የሆነ ፕሮክሲ ስርቨር የሚኖራቸዉ ሲሆን ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚከለከሉ ድረ-ገጾች በተጨማሪ በተለያዩ ድርጅታዊ ምክንያቶች በድርጅታቸዉ (በተቋማቸዉ) ዉስጥ እንዳይታዩ መከልከል አለባቸዉ የሚሏቸዉን ድረ-ገጾች ለማገድና  በተጨማሪም ወደ ድርጅታቸዉ የመረጃ መረብ የሚገቡና የሚወጡ መረጃዎችን ለመቆጣጠር ይረዳቸዋል።  ለምሳሌ  ኢትዮጵያ ዉስጥ facebookን መጠቀም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያልተከለከለ ቢሆን በርካታ ሀገር ዉስጥ ያሉ የመንግስትና የግል ተቋማትና ድርጅቶች ግን  ይህንኑ ዘዴ በመጠቀም facebook ድርጅታቸዉ ዉስጥ ባሉ ኮምፒዉተሮች እንዳይታይ (ሰራተኞች መጠቀም እንዳይችሉ) ይከለክላሉ (ያግዳሉ)። 

ይህንንም ክልከላ ተፈጻሚ ለማድረግ መንግስት አሊያም የተለያዩ ተቋማት በርካታ ዘዴዎችንና ቴክኖሎጅን በመጠቀም ክልከላዉን ማካሄድ የሚችሉ ሲሆን በዋናነት ግን የተለያየ ጥንካሬና ዋጋ ያላቸዉን የማፈኛ (የመከልከያ) ሶፍትዎሮችን በፕሮክሲ ሰርቨሮች ላይ በመጫንና እንዳይገቡ (እንዳይወጡ) የተፈለጉትን የድረ-ገጾች አድራሻ (ULR address) ዝርዝር ለነዚህ የማፈኛ ሶፍትዌሮች በመንገር ነዉ። እንግድህ እነዚህ የማገጃ ሶፍትዌሮች የሚቀመጡት ለመረጃ መዉጫና መግቢያ እንደ ዋና በር በመሆን በሚያገለግለዉ ሰርቨር ኮምፒዉተር ላይ  በመሆኑ ማንኛዉንም ወደ ዉስጥ የሚገባና ወደ ዉጭ የሚወጣ መረጃን (ድረ-ገጽ) በመመርመሪና በማጣራት (filter በማድረግ) አድራሻዉ እንዳይገቡ ከተከለከሉት የድረ-ገጽ  አድራሻዎች ዉስጥ  የተመደበ ሆኖ ካገኙት ወደ ሀገር ዉስጥ እንዳይገባና እንዳይታይ ይከለክላሉ (block) ያደርጋሉ ማለት ነዉ።  እንግድህ ጠቅለል ባለ መልኩ በርካታ ድረ-ገጾች እገዳ የሚጣልባችዉ በዚህ መልኩ ሲሆን እንደዚህ አይነት ክልከላ የተደረገባቸዉን ድረ-ገጾችን እንደት መመልከት ይቻላል ብሎ መጠየቅ አንድ ሀገር ከሚኖራት ዋነኛ የድረ-ገጽ መረጃ ማስገቢያና ማስዎጫ በር (ጉሙሩከ ጣቢያ እንደማለት) ሌላ የምንፈልገዉን መረጃ  ወደ ሀገር ዉስጥ አስገብተን ለማየት አልያም ወደ ዉጭ ለመላክ በዋናነት ካለዉ የመግቢያና መዉጫ በር በተጨማሪ ሌላ  ድብቅ በር/መሹለኪያ እንደት ማግኘት (መፍጠር) ይቻላል ብሎ መጠየቅ ማለት ነዉ። ለዚህም ብዙ አማራጮችን መጠቀምና ማንሳት የሚቻል ቢሆንም የተለመዱና ቀላል ናቸዉ ያልናቸዉን ሁለት አማራጮችን ከዚህ እንዲከተለዉ እንመልከት፡

የመጀመሪያዉና ምናልባትም ቀላሉ ሊባል የሚችለዉ  ማየት የፈለግነዉን ድረ-ገጽ በቀትታ በራሱ የURL አድራሻ በኩል ለማየት ( acess ለማድረግ) ከመሞክር ይልቅ በሌሎች ሁለተኛ ወገን  በሆኑና ለዚሁ አገልግሎት ሲባል የተፈጠሩ ድረ-ገጾችን ሽፋን በማድረግ (using website proxies) ለመመልከት መሞክር ሲሆን ይህም ማለት የሌላ እንዲገባ የተፈቀደለትንና እንዳይገቡ  ከተደረጉ ድረ-ገጾች መካከል ዝርዝሩ ያልተካተተን ድረ-ገጽ አድራሻ እንደሽፋን (የሌላ ሰዉን ID አሳይቶ እንደመግባት ማለት ነዉ) በመጠቀም የተከለለን ድረ-ገጽ እንዲገባ ማስቻል ማለት ነዉ። ኢንተርኔት ላይ የዚህ አይነት አግልገሎት የሚሰጡ ብዙ ድረ-ገጾች ያሉ ሲሆን ነገሩን በቀላሉ ለመረዳት እንድንችል ከዚህ የሚከተለዉን ምሳሌ እንመልከት

ለምሳሌ የተከለከለዉና ማየት የፈለግነዉ ድረ-ገጽ የማህበራዊ መረብ የሆነዉን facebook ነዉ እንበል እናም http://www.facebook.com የሚለዉን አድራሻ በቀጥታ የብራዉዘሩ አድሬሰ ባር (browser address bar) ላይ ታይፕ በማድረግ ለመክፈት ከሞከር ይልቅ ይልቅ በቅድሚያ http://www.spysurfing.com (ለምሳሌ ያክል የተጠቀምነዉና ከላይ የገለጽነዉን አይነት የሽፋን አገልግሎት ከሚሰጡ በረካታ ድረገጾች መካከል አንዱ ነዉ) ድረ-ገጽን በመክፈትና በፊት ለፊት ገጹ ላይ ለዚሁ አገልግሎት ተብሎ በተዘጋጀዉ ሳጥን ዉስጥ  http://www.facebook.com  የሚለዉን አድራሻ በማስገባትና በመፈለግ መክፈት ማለት ነዉ። ነገር ግን የዚህ አይነት ዘዴን መጠቀም የሚቻለዉ እንደ ተለዋጭ ፕሮክሲ በመሆን የሚያገለግለን ድረ-ገጽ (ከላይ ለቀረበዉ ምሳሌ http://www.spysurfing.com ማለት ነዉ) በአፋኞቹ በኩል የማይታወቅና እንዲታገዱ ከተደረጉ ድረ-ገጾች ዝርዝር ዉስጥ ያልተካተተ መሆን ይኖረበታል። ይህ ካልሆነ ግን አፋኞቹ ቀድመዉ ይህንኑ ድረ-ገጽ እንዳይከፈት ስለሚከለክሉት በሱ በኩል አልፈን (ሽፋን አድርገን) የምፈልገዉን ድረ-ገጽ መመልከት አንችልም ማለት ነዉ። በመሆኑም የዚህን አይነት አገልግሎት ማግኘት የሚቻለዉ በአፋኞች አይን ዉስጥ ያልገቡ ዌብ-ፕሮክሲዎችን በመጠቀምና ተከታትለዉ ሲደርሱባቸዉና ሲያግዷቸዉ ደግሞ ሌላ አድስ ዌብ-ፕሮክሲች በመፈለግና በመጠቀም ይሆናል ማለት ነዉ። ለዚህም ሲባል በቁጥር እጅግ ብዙ የሆኑና በየቀኑ የሚፈጠሩ አዳድስ ዌብ-ፕሮክሲዎች ስላሉ የሚያፍኑ አካላት ሁሉንም ማወቅና መዝጋት ስለማይችሉ አንዱ ሲዘጋ ሌላ እየቀያየርን መጠቀም እንችላለን ማለት ነዉ።

ሌላዉና ምናልባት ከላይ ከቀረበዉ አማራጭ የተሻለ እንደሆነ የሚታመነዉ ደግሞ ዌብ ሳይቶች እንደሽፋን  ከመጠቀም ይልቅ ለዚሁ አገልግሎት ተብለዉ የተሰሩ ሶፍትዌሮችን  ማዉረድና መጠቀም ነዉ።  ለዚህም ከላይ በቁጥር አንድ የተመለከትናቸዉን የድረ-ገጽ ፕሮክሲዎችን ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ  እንደ ዋነኛ ድክመት ከሚጠቀሱ በረካታ ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛዉ እነዚህ ድረ-ገፆች የሽፋን አገልግሎቱን ከመስጠት ጎን ለጎን የተለያዩ ማስታወቂያዎችን ድረ-ገጾቹን ለሚጠቀሙ ሰዎች ስለሚያስተላልፉ አላስፈላጊ የኔትወርክ መጨናነቅን የሚፈጥሩ መሆናቸዉ ነወ። ይህንን አላስፈላጊ የማስታዎቂያ ሽፋን ለማስዎገድ ደግሞ  ለዚሁ አገልገሎት ተብለዉ የተዘጋጁ ሶፍትዌሮችን በማዉረድና ኮምፒዉተራችን ላይ በመጫን እንዳማራጭ መጠቀም እንችላለን። ነገር ግን እነዚህ አይነት ሶፍትዌሮች ተጨማሪ ማስተካከያዎችን (configuration) ስለሚጠይቁ እንደላይኛዉ አማራጭ ቀላል ላይሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ የዚህ አይነት አገልግሎት ከሚሰጡ ሶፍትዌሮች መካከል ultra surf የሚባለዉ ሶፈትዌር በብዛት አገልገሎት ላይ የዋለና የተሻለ የሚባል ሲሆን ይህን ሶፍትዌር በመጠቀም የተከለከሉ ድረ-ገጾችን ለመጎብኘት ኮምፒዉተራችንን ከዚህ እንደሚከተለዉ በማስተካከል መጠቀም እንችላለን

a.     በቅድሚያ የቅርብ ጊዜ ቨርዠን የሆነዉን ultra surf ሶፍትዌር ማዉረድ (የሶፍትዌሩ ሳይዝ (መጠን) በኪሎ ባይት ደረጃ ሲሆን ዚፕድ (zipped) የሆነዉን ፋይል በቀላሉ ጉግል ላይ ultra surf የሚል ዋና ቃል  ታይፕ በማድረግና በመፈለግ ማዉረድ ይቻላል)
b.     በመቀጠል ያወረድነዉን zipped ፋይል unzip በማድረግ የሶፍትዌሩ ተፈጻሚ የሆነዉን ፋይል (excutable file) በኮምፒዉተራችን ላይ ስናሮጠዉ ( run ስናደረገዉ) connecting to the server የሚል መልዕክት (messege) የያዘ ዲያሎግ ቦክስ ይመጣልናል።
c.     በማስቀጠል sussusfully connected to the server የሚል መልዕክት እዚሁ ድያሎግ ቦክስ ላይ እስከምናይ ድረስ በትግስት መጠበቅ ይኖረብናል።
d.     sussusfully connected to the server የሚለዉን መልዕክት ካገኘን በሗላ በቀጥታ ዌብ ብራዉዘራችን በመክፈትና ተገቢዩን የፕሮክሲ አድራሻና የፖረት ቁጥር በመስጠት ማስተካከል (configure) ማድረግ ይኖረብናል። ለምሳሌ የምንጠቀመዉ ዌብ ብራዉዘር Mozila firefox ቢሆን እንደሚከተለዉ ማስተካከል እንችላለን።
                                          i.    ብራዉዘሩን በመክፈት internet options የሚለዉን option እንመርጣለን
                                         ii.    በመቀጠል ከሚዘረዘሩት ምርጫዎች መካከል advanced የሚለዉን  option እንመርጣለን
                                        iii.    ከዚያም network የሚለዉን ታብ (tab) ክሊክ እናደርጋለን
                                        iv.    በማስከተል manual proxy configuration የሚለዉን option ከመረጥን በሗላ HTTP proxy የሚለዉ ሳጥን ዉስጥ 127.0.0.1 የሚል ቁጥር እናስገባና port የሚለዉ ሳጥን ዉስጥ ደግሞ 9666 የሚል ቁጥርን  በማስገባትና ok የሚለዉን button በመጫን የተከፈተዉን ድያሎግ ቦክስ እንዘጋልን ከስር የነበሩን ድያሎግ ቦክስ ላይም  ok የሚለዉን button በድጋሜ በመጫን configure ማድረጋችንን አናበቃና ወደ ዌብ ብራዉዘሩ በመመለስ ያለማንም ከልካይ የፈለግነዉን ድረ-ገጽ በቀጥታ መመልከትና መከታተል እንችላለን ማለት ነዉ።
(ዌብ ብራዉዘራችን internet explorer ከሆነ ግን ultra surf እራሱ አዉቶማቲካሊ configure ስለሚያደርግልን ይህን አካሄድ ተግባራዊ ማድረግ ላይጠበቅብን ይችላል።)

ማስታዎሻ፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱና ሌሎች ተለዋጭ ፕሮክሲዎች ብዙዉን ጊዜ መረጃን ለማሳለፍ ዙሪያ ጥምጥም የሚሄዱና እሩቅ ሀገር ያሉ ተለዋጭ ሰርቨሮችን እንደ አማራጭ ስለሚጠቀሙ የሚኖራቸዉ ፍጥነት በጣም አዝጋሚ እንደሚሆን እሙን ነዉ በመሆኑም ብዙዉን ጊዜ የተከለከለን ነገር ግን ለማየት የምንፈልገዉን ዌብ ሳይት ከጎበኝን በሁዋላ ሌሎች መደበኛ (ያልተከለከሉ) ድረ-ገጾችን ለመጎብኘት እነዚህኑ ተለዋጭ ሰርቨሮችን ከመጠቀም ይልቅ ዌብ ብራዉዝራችን ወደ ነበረበት setting  በመመለስና መደበኛዉን ፕሮክሲ አድሬስ በመጠቀም መጎብኘት የኢንተርኔት ፍጥነታችንን ስለሚያሻሽልልን ብዙን ጊዜ ይመከራል።
------------------------------------------------------
አንድ ህዝብ አንድ ሀገር!

(ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!)

ግንቦት-2004

------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

No comments:

Post a Comment