የጠቅላይ ሚንስተር መለስ ዜናዊ በጠና መታምንና ከሚዲያና ከህዝብ አይን መሰዎር ሰሞኑን በህዝቡ ዉስጥ ለሚናፈሱ በርካታ ዉጅብሮች መፈጠር ምክንያት
ሆኗል። ተራዉ ህዝብ ይቅርና
አስተማማኝ የመረጃ ምንጮች አሉን የሚሉ ጋዜጠኞችን እንኳን ሳይቀር ለዉዥምብር የዳረገ ክስተት ነበር የሰሞኑ የጠቅላይ ሚንስተር
መለስ የመታመም ዜና። የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ ጠቅላይ ሚንስተር መለስ ዜናዊ ህክምናቸዉን አጠናቀዉ ወደ ኢትዮጵያ
መመለሳቸዉን ከታማኝ ምንጮች አረጋግጫለሁ ሲል፤ የጠቅላይ ሚንስትሩን መታመም አስመልክቶ አንዳችም ነገር ትንፍሽ ሳይል የሰንበተዉ
የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አማረ አረጋዊ በበኩሉ ጠቅላይ ሚንስተር
መለስ ህክምናቸዉን አጠናቀዉ ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸዉንና በተሻለ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ፣ ነገር ግን በቅርብ ቀን ስራ እንደማይጀምሩ
ዘግቧል። በሌላ በኩል የፈረንሳይ የዜና አገልግሎት የሆነዉ ኤ.ኤፍ.ፒ ጠቅላይ ሚንስተር መለስ ዜናዊ በጠና እንደታመሙና አሁንም
ድረስ ቤልጀም ብራሰልስ በሚገኝ ሆስፒታል ዉስጥ በህክምና ላይ እንዳሉ በዜና ዘገባዉ አሰራጭቷል።
ይኸ ሁሉ ሲሆን ግን ም/ጠ ሚንስተርና የዉጭ
ጉዳይ ሚንስተር ሐይለማሪያም ደሳለኝ ከሰጡት “ታሟል ግን ለክፉ የሚሰጥ አይደለም” ከሚል ሾላ በድፍን ከሆነ መግለጫ በስተቀር ይህንኑ በህዝቡ ዉስጥ የተፈጠረ
ዉጅምብር ለማጥራት በመንግስት በኩል የተሰጠ ይህ ነዉ ሊባል የሚችል የተብራራ ነገር እስካሁን የለም። ይህንንም ተከትሎ በተፈጠረዉ
የመረጃ ክፍተት ምክንያት የጠቅላይ ሚንስተር መለስ በጽኑ መታመም የአደባባይ ምስጠር ከመሆን አልፎ በርካቶችን በህይዎት የሉም ወደሚል
ድምዳሜ እንዲደርሱ አድርጓል። ያም አለ ይህ ግን ይህንኑ ሰሞነኛ ክስተት ተከትሎ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ የሀይል አሰላለፍ ለዉጥ
ሊኖር እንደሚችል ሲገመት ማን ምን ሊሆን ይችላል የሚለዉ ጥያቄ ግን እስካሁን ድረስ አጥጋቢ መልስ አላገኝም።
ኢህአዲግ እንዴ ኢህአዲግ ኢትዮጵያም እንዴ
ኢትዮጵያ ሆነዉ ሊቀጥሉ የሚችሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ እስካሉ ብቻ ነዉ ብለዉ ለሚያምኑ ጥቂት የመለስ አምላኪዎች የምጻት ቀን የቀረበ
ያክል የመታመሙ ዜና ጭንቀት እንደፈጠረባቸዉ ሲገለጽ በሌላ በኩል ደግሞ የህወሐት ነገረ ሰሪና አሽከርካሪ ሞተር መለስ ነዉ ለሚሉ
ሌሎች ከህወሐት ዉጭ ያሉ አካላት ደግሞ አጋጣሚዉን በመጠቀም ህወሐት
ለ21 አመታት በብቸኝነት ተከናንቦት የኖረዉን የገዢነት የስልጣን ጋቢ ቢቻል ለመግፈፍ ባይቻል ደግሞ ለመሸራረፍ እንዳቆበቆቡ በስፋት
እየተወራ ነዉ። በነዚህ ሁለት ጎራዎች የማይመደቡ ሌሎች ታዛቢዎች
ደግሞ፣ ህወሐት ድርጅታዊ የመከፋፈል አደጋ ካልገጠመዉና ሌሎች ተመሳሳይ ዉስጣዊ ችግሮቹን ተቋቁሙ ማለፍ ከቻለ ከስም ለዉጥ በስተቀር
በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ የሀይል አሰላለፍ ዉስጥ ሊፈጠር የሚችል ይህ ነዉ የሚባል አድስ ነገር ሊኖር እንደማይችል እየገለጹ ይገኛሉ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በንጉሳዊ አገዛዝ ትተዳደር በነበረበት ወቅት ሀገሪቱን በንጉሰ ነገስትነት ይመራ
የነበረዉ ንጉስ በተለያዩ ምክንያቶች ሲሞት፣ “ያለንም እኛ የሞትንም
እኛ፣ ስለ ንግሳችን ተደሰቱ ስለ ሞታችን እዘኑ” የሚል አዋጅ ነጋሪት እየተጎሰመ ለህዝቡ ይለፈፍ ነበር። ይህም እንግድህ ምንም እንኳን የሀገሪቱ እራስ የሆነዉ ንጉሰ ነገስቱ ቢሞትም
ንጉሱን ተክቶ የሀገሪቱን የንጉሰ ነገስትነት ስልጣን የሚይዘዉ የንጉሱ ቤተሰብ (ዘር) የሆነ ሰዉ (በተለይም ልጅ) በመሆኑና በዚሁ
ምክንያት ስልጣን ከንጉሱ ዘር እንዳልዎጣ ለህዝቡ ለማመላከት ሲባል ነበር “ያለንም እኛ፣ የሞትንም እኛ” የሚል አዋጅ መለፈፉ።
እንግድህ
የነዚህ ሰዎች (ምንም አድስ ነገር አይኖርም የሚሉ አካላት) መላምት እዉን የሚሆን ከሆነ ደግሞ ምንም እንኳን እንደ ድሮዉ ነጋሪት
እየተጎሰመ “ያለንም እኛ፣ የሞተንም እኛ” የሚል አዋጅ በይፋ ባይነገረም ዛሬም ሀገራችን ኢትዮጵያ በፖለቲካዊ የስልጣን ሽግግር
ረገድ ያለችበት ሁኔታ ከትናንቱ የማይለይ፣ እንዳዉም ትንሽ እንኳን የድሞክራሲ ጭላንጭል የማይታይበት የፖለቲካ አዙሪት ዉስጥ እንዳለችና
“የሞተዉም ህወሐት፣ ያለዉም ህወሐት” ከሚል የመፈክር ለዉጥ በስተቀር እስካሁን ባለፈችባቸዉ የሺ ዘመናት ፖለቲካዊና ታሪካዊ ሁነቶች
ዉስጥ ለህዝብና ለሀገር የሚሆን አንዳችም ጠብ የሚል ቁም ነገር እንዳልገበየች አመላካች ነዉ። “የሞተዉም ህወሐት፣ ያለዉም ህወሐት”
ወይስ ሌላ? ጊዜ ከሰጠን ሁሉንም በቅርብ ቀን የምናየዉ ይሆናል።
-------------------------------------------------------------------------------
-------------------------------------------------------------------------------
እጅግ ደስ የሚል ዓላማ ፡ ይዘትና አቀራረብ ያለው ብሎግ በመሆኑ በጣም ወድጅዋለሁ!!በርቱ! መልካም ሥራችሁን እግዚአብሔር ይባርክ!ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!
ReplyDelete