Thursday, July 5, 2012

በኢትዮጵያ የመጀመሪያዉ/ን…

 መቸም ኢትዮጵያ ዉስጥ አድስ የተጀመረን ነገር ወይም የነበረን አገልግሎት ሲቻል  በአለም፣ ካልሆነ በአፍሪካ እነዚህ ሁለቱ ካልተሳኩ ደግሞ “በኢትዮጵያ የመጀመሪያዉ” በሚል ተቀጥላ ማስተዋወቅ በህግ ተደንግጎ የተቀጠ ግደታ እስከሚመስል ድረስ  ከግለሰብ እስከ መንግስት ተቋማት ድረስ የተለመደ ነዉ። ምናልባትም የዚህ አይነት የማስታዎቂያ ተቀጥላዎችን በብዛት በመጠቀም በአለም የመጀመሪያዎቹ ሳንሆን አንቀርም (lol አላችሁ!)።  በእዉቀቱ ስዩም “የቤተሰቦቼ ሁለተኛ ልጅ በመሆን የመጀመሪያ ነኝ”  ሲል በአሽሙር ልክልካቸዉን እንደነገራቸዉ ማለቴ ነዉ፡፡ በርግጥ ከኢትዮጵያም አልፈዉ በአለም ደረጃ ለመተግበር ቀርቶ ለማሰብ እንኳን የሚከብዱ በርካታ ስራዎችን ቀዳሚ በመሆን ያበረከቱ አሊያም ያስተዋወቁ የትየለሌ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ እሙን ነዉ። እነዚህን ኢትዮጵያዊያንም “የመጀመሪያዉ” በሚል የማሞካሻ የማዕረግ ተቀጽላ መጠራት ቢያንሳቸዉ እንጂ የሚበዛባቸዉ አይሆንም። ምናልባትም ዛሬ ላይ ያሉ ማስታዎቂያ ነጋሪዎችም በእዉቀቱ እንዳለዉ “የመጀመሪያዉ” የሚለዉን ተቀጽላ “እግዚያብሔርም በመጀመሪያ ሰማይና ምድርን ፈጠረ” ከሚለዉ የመጸሐፍ ቅዱስ ቃል ሳይሆን ከነዚህ ኢትዮጵያዉያን የክብር ስም ላይ ይሆናል ላፍ አድርገዉ የወሰዱት። 

 

ምንም እንኳን በዘመናቸዉ “የመጀመሪያዉ” በሚል ተቀጽላ እምብዛም ባይሞካሹም (አሁን የኢህአድግ ደጋፊዎች “ አባይን የደፈሩ የመጀመሪያዉ መሪ” ምናምን እንደሚሉት ማለቴ ነዉ!) በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ “የመጀመሪያዉ” ወይም “የመጀመሪያዉን” በሚል ተቀጽላ ከሚቆለፓፐጹ መሪዎችና ግለሰቦች መካከል የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መስራች የሆኑትን እምዬ ሚንልክን የሚወዳደራቸዉ ያለ አይመስለኝም። የመጀመሪያዉ መኪና የነዱ ኢትዮጵያዊ፣ የመጀመሪያዉ ዘመናዊ ጫማ የተጫሙ ኢትዮጵያዊ፣ የመጀመሪያዉ ፎቶ አንሽ ኢትዮጵያዊ፣ የመጀመሪያዉ ኢትዮጵያዉ የሆቴል አግልግሎት ተጠቃሚ …  የመጀመሪያዉን ባንክ የመሰረቱ፣ የመጀመሪያዉን ሆቴል የከፈቱ፣ የመጀመሪያዉን ፖስታ ቤት ያቋቋሙ፣ የመጀመሪያዉን የስልክ አገልግሎት ያስጀመሩ፣ የመጀመሪያዉን የኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት፣ ጋዜጣ፣ የባቡር መንገድ፣ የቧንቧ ዉሃ አገልግሎት ወ.ዘ.ተ … እያልን መዘርዘር ብንቀጥል እንድሁ በቀላሉ አናበቃም። ነገር ግን ስለ አጼ ሚንልክ በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ቀዳሚ ሆኖ መገኘት ብዙ ብዙ የተባለለትና ተደጋግሞ የተነሳ ጉዳይ ነዉና በዚሁ እንለፈዉ። ከዛ ይልቅ ዛሬ ላዎጋችሁ የፈለኩት በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ በመሆን የተመዘገቡ ነገርግን ብዙም ስለማናዉቃቸዉ ሶሰት “የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊያን” ነዉ።

 

 የመጀመሪያዉ በአዉሮፕላን የተጓዙ ኢትዮጵያዊ

በአንድ ወቅት ቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ በእንግሊዝ ጋባዥነት የራሳቸዉ የእንግሊዞችን ወታደራዊ ልምምድ ለመመልከት በእንግድነት የመን ይገኛሉ። ትርኢቱን ጥቂት ከተመለከቱ በሗላም እንግሊዞች ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴና አብረዋቸዉ የነበሩትን ራስ እምሩን በጦር አይሮፕላን እንዲበሩ ግብዣ አደረጉላቸዉና በጦር አዉሮፕላን አጭር በረራ አደረጉ በዚህም በአይሮፕላን የበረሩ የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያዉያን በመሆን እነዚህ ሁለት ሰዎች በታሪክ ማህደር ለመዝገብ በቁ።

 

 የመጀመሪያዉ በአዉሮፕላን አደጋ የሞተ ኢትዮጵያዊ

ጥላሁን ብርሃነ ሥላሴ “የ20ኛዉ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ” በሚለዉ መጸሐፋቸዉ ስለ መጀመሪያዉ በአይሮፕላን አደጋ የሞተ ኢትዮጵያዉ ሲያዎጉን እንድህ እንደዛሬ በአሸባሪዎች ሴራ ወይም ደግሞ በመሰሪ መንግስታት ተንኮል ሳይሆን ቆሞ ሲፎክር እንደነበር እንድህ ሲሉ ያወጉናል። የጃንሆይ አጎት ደጃች ወልደ ሥላሴ ለመንግስት ሥራ ደሴ ደርሰዉ ሲመለሱ አደጋ ተፈጥሮ ቀበቶ ሳያስሩ ቆመዉ ሲፎክሩ አይሮፕላኑ ሲያርፍ ራሳቸዉን በሃይል ስለመታቸዉ ከተሳፋሪዎቹ መካከል እሳቸዉ ብቻ በአደጋዉ ይሞታሉ። ስለሆነም በአይሮፕላን አደጋ በመሞት እኝሁ የራስ መኮንን ወንድም (የአጼ ሀይለ ሥላሴ አጎት) ደጃች ወልደ ሥላሴ የመጀመሪያዉ ኢትዮጵያዊ ናቸዉ ይላሉ። እንደ እኔ እንደ እኔ ግን ደጃች ወልደ ሥላሴ የመጀመሪያዉ በአይሮፕላን አደጋ የሞቱ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆኑ ብቸኛዉ አዉሮፕላን ዉስጥ እየፎከሩ የሞቱ ኢትዮጵያዊም ይመስሉኛል።

 

 የመጀመሪያዉ ሐዉልት የቆመለት ኢትዮጵያዊ የቤት እንስሳ

ምንም እንኳን ብዙዎቻችን በአካል ባናዉቃትም የቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴን ድንክ ዉሻ ንጉሰ ነገሥቱ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተነሷቸዉን ፎቶዎችን ስንመለከት አብረን ተመለክተናታል። ይችዉ የአጼ ሀይለ ሥላሴ ድንክ ዉሻ ሉሉ ትባል ነበር። ንገሠ ነገስቱ አብዝተዉ ይወዷት ነበር። ሌላዉ ቀርቶ ለተለያዩ የሀገር ዉስጥና የዉጭ ሀገር ጉብኝቶች እንኳን ሲሄዱ ከጎናቸዉ እንድትለይ አይፈልጉም  ነበር። በወቅቱ ለአንድ ሻምበል ደመወዝ ይከፈለዉ የነበረዉን 170 ብር በወር እየተቆረጡላት ነበር እንደ ልጅ አቀማጥለዉ ያሳደጓት። ዳዱ ግን ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከሞት የሚቀር የለምና ሉሉም ተራዋ ደርሶ ሞተች። አጼ ሀይለ ሥላሴም ቤተ መንግስታቸዉ ዉስጥ በክብር እንድትቀበር ካደረጉ በሗላ ምን የመሰለ  ከእብነበረድ የተሰራ ሐዉልት መቃብሯ ላይ አቆሙላት። እናም እንግድህ ሉሉ በክብር የተቀበረችና ሐዉልት የቆመላት የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ የቤት እንስሳት ለመባል በቃች።

 

 -የማኪያቶ ወግ- 

አንድ ሀገር አንድ ህዝብ

------------------------------------------------------------------------------- -------------------------------------------------------------------------------

No comments:

Post a Comment